ከኮቪድ - 19 ጋር እየተካሄደ ያለውን ፍልሚያ በማጠንከር ሆቴል ውስጥ ወሸባ የገቡ የባሕር ማዶ ተመላሽ መንገደኞች ሁለት ጊዜ የቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ ግዴታ የሚጥል ድንጋጌ ትናንት ማምሻውን ማለፉን የቪክቶሪያ መንግሥት አስታውቋል።
በድንጋጌው መሠረት ሆቴል ወሸባ ገብተው ያሉ ተመላሽ መንገደኞች የ14 ቀናት ቆይታቸውን ጨርሰው ከመውጣታቸው በፊት በሶስተኛና 11ኛ ቀናት ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያካሒዱ ግድ ይሰኛሉ።
"በዛሬው ዕለት የሚወጡ ሰዎች ሁሉም ምርመራ አድርገዋል። ማናቸውም ከዛሬ ጀምሮ የቆይታ ጊዜያቸውን ጨርሰው የሚወጡ ሁሉ ምርመራ ያደርጋሉ። ለመመርመር ፈቃደኛ የማይሆኑ ካሉ ተጨማሪ 10 የቆይታ ቀናት ተጥሎባቸው ለ24 ቀናት እንዲቆዩ ይደረጋል" ሲሉ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ አስታውቀዋል።
ፕሪሚየር አንድሩስ ቫይረሱ ተስፋፍቶ ባሉባቸው ቀበሌዎች የቤት ውስጥ ቆይታ ገደቦችን ለመጣል እሳቤ ያለ መሆኑንም አክለው ገልጠዋል።
ዛሬ እሑድ ከተመዘገቡት 49 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ውስጥ አራቱ ምንጫቸው ያልታወቀ፤ 26ቱ በመደበኛ ምርመራ የተገኙ ሲሆን፤ የተቀሩት መንስኤያቸው እየተመረመረ ይገኛል።
አቶ አንድሩስ ከተመላሽ መንገደኞች የማኅበረሰብ ተጋቦት አለመከሰቱን ጠቁመው፤ መንግሥታቸው ቁጥሩ እየጨመረ ያለውን ቫይረስ ለመከላከል እያደረገ ባለው ግብረ ምላሽ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጠዋል።
አያይዘውም "ቤትም ውስጥ ይሁን ሆቴል፤ ተጋላጭነት አልባ ሞዴል መተግበር አይቻልም። ምንም ይደረግ ምን። ከቶውንም 100 ፐርሰንት ተጋላጭነት አልባን ግብር ላይ ማዋል አይቻልም"
"ተግዳሮቱ ልክ እንደ ደን ቃጠሎ ነው። ማድረግ የምንችለው ተስፋፍቶ እንዳይዛመት መገደብ ነው። ሁነኛው መንገድም ምርመራና በቫይረሱ የተያዙትን ተከታትሎ ማግኘት ነው" ብለዋል።
በማከልም፤ ከጃኑዋሪ 1 ጀምሮ ቪክቶሪያ 780,000 ምርመራዎችን ያካሄደች መሆኗንና ከዛሬ እሑድ ጀምሮም ምርመራው በምራቅ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የቫይረስ ምርመራዎች ይካሄዱ የነበሩት በአፍንጫ ቀዳዳዎችና ጉሮሮ በኩል ናሙና በመውሰድ ነበር።
የጤና ሠራተኞች በተለይ ኪሎር ዳውንስና ብሮድሜዶውስ ቀበሌዎች በመገኘት ቤት ከቤት ምርመራዎችን እያካሄዱ ነው።
ለነዋሪዎቹ ቅዳሜ ዕለት ምርመራ እንዲያካሂዱ አስቸኳይ የስልክ ጽሁፍ መልዕክቶች ተላልፎላቸዋል።
አቶ አንድሩስ ሰዎች ለቫይረሱ መስፋፍት የተወሰኑ ባሕላዊ ቡድናት ወይም የማኅበራዊ-ምጣኔ ሃብት የመደብ ጀርባ ያላቸውን ለይተው ጣታቸውን ከመጠቆም እንዲቆጠቡ ሲያሳቡ፤
"ቫይረሱ የትውልድ ሥፍራን አይለይም፤ ጸላዮች ሁኑ ወይም ለማን እንደምትጸልዩም ለይቶ አያጠቃም" ብለዋል።
የቪክቶሪያ እስልምና ምክር ቤት የተወሰኑ የሚዲያ ዘገባዎች የሙስሊም ማኅበረሰቡን ያላንዳች ማስረጃ ለይተው ለሰሞኑ የኮሮናቫይረስ መስፋፋት ጣት ማመላከቻ አድርገውናል ሲል ተቃውሞን አሰምቷል።