የጀምበር ስርቀትና ጥልቀት
በአያሌዎች አዕምሮ ስለ አውስትራሊያ ሲታሰብ ተከሳች ምስሎቿ በእጅጉ በሀብት የበለፀገች፣ ዜጎቿ የተሟላ ኑሮ ያላቸው፣ የሥራ አጥነት ቁጥር ዝቅተኛ የሆነባት፣ ድንቅ የማኅበራዊ ድጎማ ፕሮግራሞች ግብር ላይ የሚውሉባት ማለፊያ ሀገር ተስላ መታየቷ እውነት ነው።
ምስሎቹ እውነታን የተላበሱ መሆናቸው ሐቅ ነው።
ሆኖም፤ በየዕለቱ ጀምበር ስትጠልቅ በአውስትራሊያ ስታቲስቲክ ቢሮ የ2021 ዋቤ መሠረት ከ122 ሺህ በላይ ዜጎቿ ማደሪያ አልባ ናቸው።
እንደ አቶ ጊቤና ወ/ሮ መቆያ አራት ሕፃናት ሁሉ፤ መጠለያ አልባ ከሆኑ ሰባት አውስትራሊያውያን አንዳቸው ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች ነው።
በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ የእራሳቸው መኝታ ክፍል የሌላቸው ግለሰቦች በመጠለያ አልባነት በሚነቀሱባት ሀገረ አውስትራሊያ ከአራት ሕፃናት ልጆች ጋር በአንዲት ድንኳን ለመጠለል መዳረግ ለኅሊና ፈታኝ ነው።
አቶ ጊቤና ወ/ሮ መቆያ በሕፃናት ደኅንነት ጥበቃ ኃላፊዎች ቤት ፈልገው ልጆቹን ማስጠለል ካልቻሉ ልጆቻቸው በመንግሥት ጥበቃ ስር እንደሚውሉ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።
ልብ ሰባሪ እንክርታቸው ግና የአንድ ሩህሩህ ባልና ሚስት ልብን ለማራራት አላነሰም።
የቀናት መጠለያ
መልካሞቹ ኢትዮጵያውያን አቶ ደምሴ ደስታና ባለቤታቸው፤ በራቸውን ከፍተው፣ የእንግዳ ማረፊያ ወለላቸውን ለአቶ ጊቤና ወ/ሮ መቆያ ቤተሰብ ለቀናት ፍራሽ መዘርጊያ ቸረዋል።

Demssie Desta. Credit: SBS Amharic
እንደ አቶ ደምሴ ደስታና ባለቤታቸው ያሉ በርካታ አዛኝ ልቦች፣ ታዳጊ በሮችና የአስተዋይ አዕምሮ ስብስብን በእጅጉ ይሻል።
የአቶ ጊቤና ወ/ሮ መቆያ ታምራት የተማፅኖ ጥሪዎችም እኒህ ናቸው።
መንፈስ አዋኪው ክስተት ለኢትዮጵያውያኑ ማኅበረሰብ አባላት ልባዊ መወያያ፣ መፍትሔ ማፈላለጊያና ለድርጊት መነሻ አስባብ ሊሆንም ይችላል።