የማኅበረሰብ ስፖርትን የመቀላቀልዎ ማለፊያነት

Soccer game_Melb Social Soccer.jpg

Soccer game Credit: Melbourne Social Soccer

መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴ ለመልካም የአካል፣ የአዕምሮ ጤናና ደኅንነት አስፈላጊ ነው። የማኅበረሰብ ስፖርት በጠገግ ያልተሸበበ አካታችና ትሩፋቶቹም በፍልሰት በቅርብ ለመጡቱ አያሌ ነው።


የማዘጋጃ ቤት እግር ኳስ ሜዳ ከተማ ውስጥ መታደሚያ፣ የባሕላዊ ልውውጥና ዝንቅነት ሥፍራ ሆኗል።

የሜልበርን ማኅበራዊ እግር ኳስ እየጎለበተ የመጣው አዘቦታዊ ያልሆነ አንድ ቡድን 'የቅዳሜ ኳስ መጫወቻን ከመፈለግ' ተነስቶ እንደሁ ተባባሪ መሥራቹ ማይክል ማካርተር ይናገራሉ። ክለቡ አሁን ቪክቶሪያ ውስጥ ካሉት ትላልቅ የማኅበራዊ እግር ኳስ ክለቦች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

አብዛኛዎቹ ተጫዋቾቹም ዓለም አቀፍ ተማሪዎች፣ ጓዘ ቀላል ተጓዦችና አዲስ በፍልሰት የመጡ መሆናቸው አንዱ የሕልውናው ዋቤ ሆኗል። አገር ቤት ሳሉ ይከውኑት የነበረውን ለማድረግ ከአደጋ ተጋላጭነት የራቀ፣ የወዳጅነትን መንፈስ የተላበሰ ከሰዎች ጋር መገናኛ ሥፍራን ፈልገው ማግኘታቸውን አቶ ማካርተር ያስረዳሉ። .
ልምምድ አናደርግም። ቅዳሜ ዕለት በሥፍራው እንገኛለን ወይም በሳምንቱ ውስጥ አንዱን ቀን ብቅ እንላለን። አዝናኝ ነው፣ ፉክክር የተመላበት ጨዋታ ነው። ሆኖም የምንጫወተው ለአንድ የላቀ ዓላማ አይደለም።
ማይክል ማክካርተር፣ የሜልበርን ማኅበራዊ እግር ኳስ ተባባሪ - መሥራች
ጨዋታዎቹን እስከ $10 የሚደርስ ክፍያን በመፈጸም መሳተፍ ይችላሉ፤ ምንም ዓይነት የክህሎት ወይም የአካላዊ ጥንካሬ ደረጃን አይጠይቁም።ለኢንሹራንስ ሲባል ዕድሜዎ የግድ 18 ዓመት የሞላ መሆን አለበት። የሜልበርን ማኅበራዊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ዕድሜያቸው ከ 20ዎቹ እስከ 50ዎቹ ባሉት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው።

ሰዎች ተሳትፎ የሚያደርጉት ተለምዷዊ ከሆነው የአካል ጥንካሬ ምክንያት ባሻገር ነው። በርካታዎቹ ከጨዋታው በኋላ ማኅበራዊ ግንኙነት ያደርጋሉ፣ የቅዳሜው የሴቶች ቡድን በጣሙን የጠበቀ ወዳጅነት ላይ ደርሷል።
Women playing basketball.jpg
Women playing basketball Credit: Getty Images/Peathegee Inc

ስፖርት ለመድብለባሕላዊ ሴቶች ያለው ትሩፋት ምንድነው?

እንደ መሥራችዋ ሞሊና አስትሃኒ ላሉቱ ምስጋና ይግባቸውና የመድብላባሕላዊ ሴቶች በስፖርት ውስጥ ማለፊያ መንገዶችን ፈልገው አግኝተዋል።

በስፖርት አማካይነት መድብለባሕላዊ ሴቶች በስፖርት ውስጥ ራስን የማብቃት፣ የደኅንነትና ማኅበረሰባዊ ትስስሮሽን ግንዛቤ ያስጨብጣሉ። ለማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና የተደራሽነት መሰናክሎችን ገደብ ያበጃሉ።

ወ/ሮ አስትሃኒ “እኒህ ከባሕል - ባሕል ቢለያዩም በአብዛኛዎቹ ማኅበረሰባት ውስጥ ፆታዊ ልማዶችና የሴቶች በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሏቸው ባሕላዊ ሚናዎች ናቸው”

"አሁን በስፖርት ክለቦች ውስጥ ያለው ባሕል በወንዶች፣ አንግሎ ሳክሰን፣ አልፎ አልፎም በአልኮል መጠጥ የሚነዳ ነው። ይህ መድብለባሕላዊ መደብ ጀርባ ላላቸው ሴቶች አዋኪ ነው። ምጣኔ ሃብታዊ መሰናክሎችም ስላሉ ስፖርት ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ነገሮች ውስጥ የሚሰፍረው በስተመጨረሻ ነው" ብለዋል።
Kayakers.jpg
Kayakers Credit: Getty Images/Robyn Wood
የሜልበርን ማኅበራዊ እግር ኳስ የሴት ዳኞችንና አሰልጣኞችን፣ ረጅም ልብሶችን ወይም ሂጃቦችን ለብሰው ለሚጫውቱ ሴቶችን ብቻ ለሚጠቀሙ፣ ለሴቶችና ልጆች አመቺ የሆኑ እንቅስቃሴዎችንና በስፖርት አስተዳደር ውስጥ በርካታ ሴቶችን ያቀፉ ተነሳሽነቶች ላሏቸው ድጋፎቹን ይቸራል።

ወ/ሮ አስትሃኒ ስፖርትን አውስትራሊያዊ የኑሮ ዘይቤንና ሥራን በማቻቻል ረገድ ለሚከውኑ ሴቶች ከልብ በመነጨ ስሜት ድምጻቸውን ያሰማሉ።
በራስ መተማመንን፣ የውስጣዊ መንፈስ መነቃቃትና ራስን ማብቃትን ይቸርዎታል። ራስን ከመነጠል፣ በአዲስ አገር ለድባቴ ከመዳረግ፣ በስፖርት ቡድናት በኩል ወዳጅ ይፈልጉ፣ ጓዳዊነትን ያዳብሩ፣ እገዛን ያግኙ። ጥንካሬና በራስ መተማመን አንዳንዴ ጉስቁልና ከተመላበት ግንኙነቶች ይመነጫል። እንዲሁም በተወሰኑ ባህላት ውስጥ ያሉ ፆታዊ ልማዶችን ይገዳደራል።
ሞሊና አስትሃኒ፣ የመድብለባሕላዊ ሴቶች በስፖርት ውስጥ መሥራች
Community Soccer_Melb Social Soccer.jpg
Community soccer Credit: Melbourne Social Soccer

ስፖርት ለወጣቶች ያሉት ፋይዳዎች ምንድናቸው?

እንደ ያሉ ድርጅቶች ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 25 ለሆነ አዲስ ለመጡ ወጣቶች የአብሮነት ስሜትን ለመገንባትና ከአካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ግንኙነቶችን ለማዳበር የሚያስችሉ የስፖርት ፕሮግራሞችን ያካሂዳሉ።

የመድብለባሕላዊ ወጣቶች ማዕከል የስፖርቶችና መዝናኛዎች ፕሮጄክት መኮንን ጄይ ፓንቻል፤ ስፖርት በአውስትራሊያ ኅብረተሰብ ውስጥ አንዱ ጥብቅ አካል እንደሆነ ሁሉ ስለ አካባቢ ማኅበረሰብም ጥሩ ግልፅ ግንዛቤ አስጨባጭ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
ፋይዳዎቹ አዲስ ጓደኞችን ማፍራት፣ በአካባቢ ስፖርት ክለቦች አማካይነት የአካባቢ የሥራ ዕድሎችን የማግኘት፤ እንዲሁም ለወጣቶች ታላቅ አካላዊና አዕምሯዊ መሳሪያነትን ያካትታል።
ጄይ ፓንቻል፤ የመድብለባሕላዊ ወጣቶች ማዕከል ስፖርቶችና መዝናኛዎች ፕሮጄክት መኮንን
አንዱ የመድብለባሕላዊ ወጣቶች ማዕከል ከትምህርት ሰዓት በኋላ የስፖርቶች ተነሳሽነት አካል የሆነው የሂዩም አካባቢ የወጣቶች ሽግግር እገዛ ፕሮግራም የቤት ውስጥ እግር ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስና ዋናን ከሚሰጡ የአካባቢ የመዝናኛ ማዕከል ጋር በመተባበር እገዛ መቸር ነው።

ማዕከሉ ለወጣቶች የስፖርት ሙያ ፈሮች መቅደድን ዓላማው በማድረግ ዕውቅና ያለው የእግር ኳስና ቅርጫት ኳስ ዳኝነት ኮርሶችን ይቸራል።

የመድብለባሕላዊ ወጣቶች ማዕከል ስፖርት ፕሮግራሞች ሁሉንም አካታች፣ ሁሉንም ዓይነት ክህሎቶች የሚደግፍ ነው። የግብረአካል ጉዳተኞችንም የሁሉም ዓይነት ክህሎቶች ፕሮግራሞች ካሏቸው ከዊልቸር የቅርጫት ኳስ፣ የቪክቶሪያ ግብረአካል ስፖርቶችና አውስትራሊያን ተቀባይ ሽርካዎቹ ጋር ያገናኛል።
Running group.jpg
Running group Credit: Getty Images/Belinda Howell

ለእርስዎ የሚሆን ስፖርትን መፈለግ

የማኅበረሰብ ስፖርት በአብዛኛው የሚካሄዱት በነፃ ወይም ዝቅተኛ በሆነ ክፍያ ነው።

ወጣት ከሆኑ ትምህርት ቤትዎ ስለ አካባቢ ማኅበረሰብ ማለፊያ ዕውቀት ያለው በመሆኑ ከዚያ መጀመሩ ጥሩ ነው። ጓደኞችዎ እንደምን በአካባቢው ባሉ ተቋማት ውስጥ ሊገቡ እንደቻሉም ይጠይቁ።

ማዘጋጃ ቤቶች በሁሉም ዕድሜዎች ያሉና የተለያዩ ክህሎት ደረጃ ያሉትን ሁሉ ከአካባቢ ክለቦችና እንቅስቃሴዎች ጋር ያገናኛሉ።

እርግጥ ነው፤ ማኅበራዊ ሚዲያ አንዱ ትልቅ ምንጭ ነው።

አቶ ማይክል ማክካርተር “በርካታ ሰዎች ፈልገው ያገኙን በ 'Meet Up' በኩል ነው”

“በዚያ በኩል ሊመዘገቡና በየሳምንቱ የጨዋታ ክፍያዎን ሊፈጽሙ ይችላሉ” ይላሉ ባይ ናቸው።

ከድራጎን ጀልባ እስከ የቤትውስጥ የራኬት ጨዋታዎች አማራጮቹ መጠነ የለሽ ናቸው።

ሞሊና አስትሃኒ በበኩላቸው “የብስክሌት ቡድኖችን የሚያካሂዱ ድርጅቶች አሉ። የደንጉዞ አውስትራሊያ፣ የመናፈሻ ሩጫም አሉ።”

“የማኅበረሰብ ቡድናት አንዳንዴ ስፖርትን ከማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ያያዛሉ። ስፖርት የእርስዎን ፍላጎት ያረካ እንደሁ ለማወቅ የአካባቢዎን አንድ ቡድን ፈልገው ይቀላቀሉ” ብለዋል።

ወጣትም ይሁኑ በዕድሜ የገፉ አዘውትሮ እንቅስቃሴዎችን ማካሔድ ለማንኛውም ሰው ጤንነት ጠቃሚ ነው። ይሁንና እንደ ዕድሜዎና ችሎታዎ ሁሌም አዲስ ልምምድ ከመጀመርዎ በፊት የጤና ክብካቤ ባለሙያን ያማክሩ።

ለተጨማሪ መረጃ ወይም በአካባቢዎ ያሉ የስፖርት ክለቦችን ፈልገው ለማግኘት ድረገጽን ጎብኙ።

Share