የሙዋዕለ ሕፃናት ሕመምን መቋቋም፤ ጥቆማዎች ለአዲስ ፍልሰተኞችና የመጀመሪያ ጊዜ ወላጆች

Australia Explained Childcare sicknesses

Early childhood edukesen hemi wan must long Ostrelea from hemi kivim ol parents taem blong go bak long wok. Credit: Hispanolistic/Getty Images

ሙዋዕለ ሕፃናትን ቀደም ብሎ የመጠቀም ውሳኔ ለልጅዎና ለእርስዎም የሥራ መስክ ያግዛል። ይሁንና፤ በተለይም የበርካታ አዲስ ፍልሰተኞችን ወይም የመጀመሪያ ጊዜ ወላጆች የቤተሰብ ሕይወቶችን የማስተጓጎል አቅም አለው። አዲስ ፍልሰተኞች ይህን ተግዳሮት በውል ለመቋቋም ራሳቸውን እንደምን ማሰናዳት ይቻላቸዋል?


አንኳሮች
  • ሕፃናትንና ታዳጊ ሕፃናትን ወደ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ተቋማት ሳይዘገዩ ቀደም ብሎ መውሰድ ወላጆች ወደ ሥራ ገበታቸው ፈጥነው እንዲመለሱ እንደሚያግዝ ይመከራል
  • የመጀመሪያ ጊዜ ወላጆችና አዲስ ፍልሰተኞች በተለይ አብዝቶ በሙዋዕለ ሕፃናት ተደጋጋሚ ሕመም እየተፈተኑ እንዳለ ይሰማቸዋል
  • የተወሰኑ ከሴንተርሊንክ ድጎማ ለማግኘት መመዘኛዎችን የማያሟሉ ፍልሰተኞች ሙሉ የሙዋዕለ ሕፃናት ወጪዎችን በራሳቸው ለመሸፈን ግድ ይሰኛሉ ፍልሰተኞች
  • የታመመ ሕፃንን ከሙዋዕለ ሕፃናት ማዕከል ማስቀረት ለሌሎች ሕፃናት የክብካቤ ግዴታን መከወን ነው
ፍልሰተኞች አውስትራሊያ ውስጥ የቤተሰብ ድጋፍ ስለሌላቸው ልጆቻቸውን ወላጆቻቸው ዘንድ አድርሰው ለቤተሰባቸው ገቢ ለማስገኘት ዕድሉ አይኖራቸውም።

አውስትራሊያ ውስጥ ሠራተኛ ወላጆች ወደ ሥራ ገበታቸው መመለስ እንዲችሉ ልጆቻቸውን ወደ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲያስገቡ ይመከራል።  

የሕፃናትና ታዳጊ ሕፃናት ወደ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አዘውትሮ መመላለስ በቀላሉ በሕመም ያለመጠቃት የውስጠ ሰውነት አቅምን እንደሚገነባና ለመደበኛ ትምህርት ቤት ማኅበራዊና የቀለም ትምህርት ቅበላም እንደሚያዘጋጃቸው ይነገራል።

ሆኖም፤ ሕፃናትና ታዳጊ ሕፃናት የረጅሙን ሕይወታቸውን ጉዞ በሙዋዕለ ሕፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርታቸውን ሲጀምሩ፤ እንደ አዕምሯቸው ሁሉ የውስጠ ሰውነት ሕመም መከላከያ አቅማቸውም አብሮ መጎልበት ይጀምራል።  

በዓይን፣ አፍ፣ ሆድ ዕቃና ገላ ላይ ከሚገኙ ማይክሮቦች ጋር ተገናኘተው መታገል የሚጀምሩትም እዚህ ነው።
Australia Explained Childcare sicknesses
Doctors often recommend that most infections will subside without specific medical treatment.  Credit: The Good Brigade/Getty Images
ከሙዋዕለ ሕፃናት ከሚመጡ ሕመሞች ጋር ቀደም ያለ ተሞክሮና የአውታረ መረብ ድጋፍ ለሌላቸው የመጀመሪያ ጊዜ ወላጆች አንድም ለድንጋጤ አለያም ፈጥነው ለድካም ተጋላጭ ይሆናሉ።  

ጄዮቲ ሳንዱ በምዕራብ ሜልበርን የቅድመ መደበኛ ትምህርት አስተማሪ ናቸው።

ወላጆች ልጆቻቸውን ከማስመዝገባቸው በፊት በገለጣ ክፍለ ጊዜ ስለ ሁኔታው ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
ሕፃናት ለሁለት አዋቂ ሰዎች ብቻ ተጋላጭ የሚሆኑበት የቤት ውስጥ ሁኔታ ለደህንነታቸውን በጣሙን ጥሩ ነው። ይሁንና በቅድመ መደበኛ ትምህርት ሁኔታ፤ ሕፃናት ለበርካታ ሕፃናትና አዋቂዎች ተጋላጭ ይሆናሉ። እናም በተወሰነ ዓይነት ሕመም መያዝ የተለመደ ነገር ነው።
ጄዮቲ ሳንድሁ
አክለውም፤ አብዛኛዎቹ የሙዋዕለ ሕፃናት ሕመሞች አሳሳቢ እንዳልሆኑ ገልጠው፤ ሆኖም ጥቂቶቹ ብርቱ ተላላፊ ሕመሞች ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላክተዋል።

ከሙዋዕለ ሕፃናት በርካታ ተላላፊ በሽታዎች ያገኟቸውን ሕፃናት የመረመሩት የሜልበርኑ ጠቅላላ ሐኪም አሚር ሳኢዱላህ ሲናገሩ፤

“ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት የሆኑ በርካታ ልጆችን እናክማለን... ክረምቱ ውስጥ የገጠሙን የላይና የታች መተንፈሻ አካልና የጆሮ ውስጥ ሕመሞች ናቸው። በተጨማሪም በጋ ውስጥ በርካታ የሆድ ውስጥ ሕመምተኞች ይገጥሙናል”

“ከ 100 ያህል የሙዋዕለ ሕፃናት ልጆች ውስጥ ከ 20-30 ያህሉ እንዲህ ያሉ ተላላፊ ሕመሞች አዘውትረው ያገኟቸዋል” ብለዋል።
Australia Explained Childcare sicknesses
New migrants often face extra challenges when their child becomes ill, due to lack of support network. Credit: MoMo Productions/Getty Images
ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ሙዋዕለ ሕፃናት ማዕከል መመላለስ የጀመረ የ18 ወር ወንድ ልጅ ያላትና ለመጀመሪያ ጊዜ ለእናትነት የበቃችው ኒኪታ ስለ ተሞክሮዋ ስትናገር፤

“ልጃችን ወደ ማዕከል የሚሔደው በሳምንት አንድ ጊዜ ነው… ለሁለት ጊዜያት ያህል ብርቱ ጉንፋን ይዞት ነበር። ፓራሲታሞልና አይቢዩፕሮፌን ሊያሽለው ባለመቻሉ ጠቅላላ ሐኪሙ አንቲባዮቲክስና ስቴሮይድ አዝዞለታል። ሌላው ቀርቶ የእጅ-እግር-እና-አፍ በሽታ ወደ ቤት ይዞ መጥቷል” ብላለች።

በሥራ ቀን ሥራ ገበታ ላይ ሳሉ ተጠርተው ልጆቻቸውን ከሙዋዕለ ሕጻናት ማዕከል እንዲወስዱ መጠየቅ በራሱ ለወላጆች አበሳጭ ጉዳይ ይሆናል።  

ሕፃን ልጃቸው በየጊዜው የሚታመም ከሆነና አሠሪዎቻቸውን ከሥራ ለመቅረት ፈቃድ መጠየቅ ወይም ከንግድ ሥራ መስተጓጎል ለወላጆች አሳሳቢ ነው።  
እንደ እኛ ያሉ አዲስ ፍልሰተኞች የልጆች ክብካቤ ድጎማ መመዘኛን አናሟላም። እናም ሙሉ ወጪውን መሸፈን የእኛ ኃላፊነት ይሆናል። እኛን በተመለከተ የምንከፍለው $125 ነው። ልጅዎ በመታመሙ ሳቢያ ወደ ማዕከሉ ባይሔድም፤ ሙሉ ወጪውን መክፈል ግድ ነው። ያ ደግሞ ተጨማሪ ሕመም ነው።
ኒኪታ
ዶ/ር ሳኢዱላህ "ሕመምተኛ ሕፃን" የሚባለው እንደምን ያለ ሕፃን እንደሆነ ሲያስረዱ፤  

“አንድን ልጅ ከአፍንጫው ንፍጥ ስለወረደ ብቻ ወደ ቤት መመለስ በቂ ምክንያት ነው ብዬ አላስብም። ለምሳሌ፤ እንደ ትኩሳት፣ ሳል፣ ወይም ታላቅ ወንድም ወይም እህት የጉሮሮ ሕመም ይዞኛል ብሎ ያለ ከሆነ ወይም ሕፃኑ በግልፅ የሚታይ የሕመም ምልክት ከታየበት ወደ ቤት ሊላክ ይገባዋል ብዬ ድጋፌን እሰጣለሁ” ብለዋል።

ዶ/ር ሳኢዱላህ የትኩሳት መጠኑ (ከ39 እስከ 40 ዲግሪዎች) የደረሰ ከፍተኛ አጋላጭ የተላላፊ በሽታ ምልክት፣ ከተንጠባጣቢ ንፍጥ ጋር የተያይዘ ፈሳሽን የአለመውሰድ ብርቱ ሁኔታ፣ ተቅማጥ፣ ማስመለስ ወይም ማናቸውም ዓይነት ማሳከክ የግድ በጠቅላላ ሐኪም ሊመረመር እንደሚገባ ያሳስባሉ።

አንድን በሕመም የተያዘ ሕፃን ቤት ውስጥ እንዲቆይ የማድረግ ጠቀሜታን አስመልክተው ወ/ሮ ሳንዱህ ሲያብራሩ፤

“ወላጆች ከሥራ ፈቃድ ወስደው ከሕመምተኛ ልጃቸው ጋር አብረው መሆን እንዳለባቸው አውቃለሁ፤ ይሁንና ያ ከልጁ ተመራጭ ጥቅም አኳያ ነው… ልጅ በጣሙን ሲታመም ወላጆች ወደ ሆስፒታል ቢወስዱትም፤ ከሕመም ማገገም ግና ጊዜን ይወስዳል” ብለዋል።

አያይዘውም፤ አንድ የታመመን ልጅ ከሕፃናት ክብካቤ ማዕከል ማስቀረት ለሌሎች ልጆችና ለተቋሙም የክብካቤ ሚናን መወጣት ነው እንደሁ አስገንዝበዋል።

በጉንፋን ወይም የአንጀት ሕመም ካደረበት ልጅ ርቀትን መጠበቅና እጅን ቶሎ ቶሎ መታጠብ እንደሚገባ ይመከራል።
Australia Explained Childcare sicknesses
Frequent handwashing and keeping a safe distance from a child suffering from flu or gastro is advised.  Credit: Maskot/Getty Images/Maskot
ዶ/ር ሳኢዱላህ የተመጣጠነ ምግብና ወቅትን የጠበቀ ክትባት ለልጆች አስፈላጊ መሆኑን ሲያሳስቡ፤

“በርካታ እኛ ዘንድ ሊታከሙ የሚመጡ ልጆች ምርጫ አብዢ አዋኪ በላተኞች ሲሆኑ፤ ከተመጣጠነ ምግብ አመጋገብ ማነስ የተነሳ የብረትና የቫይታሚን ዲ ማነስ ተጠቂዎች ናቸው። እናም፤ አጋዥ የተመጣጠነ ምግብ በኪኒን ወይም በፈሳሽ መልክ ቢወስዱ የውስጠ ሰውነት የመከላከል አቅማቸውን ያጎለብታል፤ እንዲሁም ለተላላፊ በሽታዎች የመጠቃት እጋጣሚያቸውን ይቀንሳል”

“ሌላው የልጅነት ክትባቶች ናቸው… ለተከተቡ ልጆች መከላከልን ያደርጋሉ እንዲሁም በተወሰኑ የሕክምና አስባብ ላልተከተቡትም እንዲሁ" ብለዋል።

አብዛኛዎቹ አውስትራሊያ ውስጥ የሚገኙ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ማዕከላት በፌዴራል መንግሥቱ የተመደቡ ክትባቶችን ይደግፋሉ።

ወ/ሮ ሳንድሁ ይህንን አስመልክተው፤

“የተወሰኑ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲከተቡ አይሹም። እኛ ያን በተመለከተ የተለዩ ደንቦችና መመሪያዎች አሉን። የሕፃናት ክብካቤ ማዕከሉ ውስጥ ተላላፊ በሽታ ቢከሰት፤ ያልተከተቡ ልጆች ወላጆች ልጆቻቸውን ቤታቸው ውስጥ እንዲያቆዩ ምክረ ሃሳብ እንሰጣለን። ስለምን ያን የሚቋቋም የውስጠ ሰውነት መከላከያ የላቸውምና” በማለት አስረድተዋል።

አበክረውም ልጆች የውስጠ ሰውነት መከላከል አቅማቸውን ለማጠናከር ከቤት ውስጥ የእንቅስቃሴ ሥፍራዎች ይልቅ እንደ መናፈሻዎችና የመጫዎቻ ሥፍራዎችን የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ አካባቢዎች እንዲያዘወትሩ ይመክራሉ። .

በመላው አውስትራሊያ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ማዕከላት የሚከተሉት የመመሪያ መፅሀፍ ነው።

የታተመው በብሔራዊ ጤናና የሕክምና ምርምር ምክር ቤት ሲሆን፤ የመመሪያ መፅሐፉ የተላላፊ በሽታ ቁጥጥርንና የሕመም ምልከታን አስመልክቶ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ማዕከላት ሊከተሏቸው የሚገቡ ፕሮቶኮሎችን የሚያብራራ ነው።


Share