"በዙሪያችን ያለውን ሐዘን፣ ፍርሃት፣ ቅያሜና ሽሽት ከመድገም፤ ሕዝብ ማየት ያልቻለውን እንዲያይ፤ መስማት የተሳነው እንዲሰማ ባደረግ እመርጣለሁ" አርቲስት ወርቅነህ በዙ

Workneh Bezu 1.jpg

Artist Workneh Bezu and his one of 'Dream with Saints' paints. Credit: W.Bezu

ሰዓሊ ወርቅነህ በዙ፤ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታትበፅልመት ውስጥ ፍካትን፣ በዕዝነ ልቦና ውስጥ ሰመመናዊ ሐሴትን በምናብ አዛንቆ በደማቅ ሕብረቀለማት በተዋደዱ የቅብ ሥራዎቹ የአያሌዎችን ቀልብ ማርኳ ቆይቷል። የጥበብ ሥራዎቹም፣ ከአገር ቤት እስከ አጎራባች አፍሪካ፤ ከአውሮፓ እስከ ሰሜን አሜሪካ ባሉ የሥነ ጥበብ አዳራሾች እንደምን ለታይታ እንደበቁለት ይናገራል።


ውልደትና ዕድገት

ሰዓሊ ወርቅነህ በዙ ትውልዱ አዲስ አበባ፤ ዕድገቱ ላሊበላና አዲስ አበባ ነው።

በልጅነቱ የስዕል ፍቅር ያደረበት ገና አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነው። ያኔ ሕብረተሰብና ሳይንስ መፅሕፍት ላይ በደማቁ የሠፈሩ ምስሎች ቀልቡን ሳቡት።

እነሱኑ አስመስሎ መሳል ጀመረ።

ከፍ ሲል ከእርሳስ ወደ ቅብ ሥራ አደገ።

የጥበብ ዓለም

ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በዘመናዊ የሥነ ጥበብ ዲዛይንና ቅብ ባለ ዲግሪ ሆነ።

ከዩኒቨርሲቲ ምረቃ በኋላ ከአራት አብሮ ተመራቂ ጓደኞቹ ጋር ሆኖ 'የአበሻ አርት ስቱዲዮ' በሚል መጠሪያ አንድ የጥበብ ማዕከል አቆሙ።

የጥበብ ጉዟቸውን በጋራ መጓዝ ጀመሩ።

ጊዜ፣ ዕውቀትና ተሞክሮ በጣምራ ውስጡ ሲጎለብቱ የራሱን የስዕል ስቱዲዮ መሠረተ።

ለበርካታ የመስኩ የጥበብ ሰዎች ሙያቸው በሚያስገኝላቸው ገቢ ብቻ መተዳደር አዋኪ ቢሆንም፤ ወርቅነህ ግና የስዕል ሥራዎቹ በሚያስገኙለት ገቢዎች ብቻ ኑሮና ሙያውን እየደጎመ ከዘለቀ ሁለት አሠርት ዓመታት ተቆጥረዋል።
Dream of Saints 2.jpg
'Dream of Saints' by Artist Workneh Bezu. Credit: W.Bezu
ሥነ ጥበብና ሕብረተሰብ

አገር ቤት የሥነ ጥበብ ዕድገት ደረጃ በራሱ አቅምና ፍጥነት አዝግሞ ቢጓዝም፤ ጥበብና ሕዝብን የሚያዋድዱ ባለሙያተኞች እጥረት ወርቅነህ ቅር ከሚያሰኙ የመስኩ ሳንካዎች አንዱ ነው።

ይህንንም ሲያስረዳ "ኢትዮጵያ ውስጥ ሥነ ጥበብን በባለሙያ መነፅር ገምግመው ኪናዊ ሂስ የሚያቀርቡ፣ አጉልተውና አድምቀው የሚያመላክቱ፣ በግልፅ ያልታዩትን ለሕብረተሰቡ የሚያስረዱ ፕሮፌሽናል ሃያስያን የሉንም"

"ስዕሉ ራሱ ጮኾ መግለፅ ያልቻለውን ከአርቲስቱ ሲሰማ የበለጠ ይረዳዋል። ጥበቡን ይወደዋል። አንድ ሰው ጥበብን ሲያደንቅ፣ ሲወድ ኃጢአትን ይፀየፋል" ይላል።
Apple.jpg
Credit: Workneh Bezu

አያይዞም "ሙሉ በሙሉ የተዳፈነም ባይሆን የአርቲስቶችን የጥበብ ሥራዎች ወደ ጋለሪና ሙዚየም የሚያደርስ ኢንስቲትዩት የለንም"

"ኢትዮጵያውያንም ሆኑ አፍሪካውያን አርቲስቶች እርስ በእርሳቸው ተገናኝተው የሚወያዩበት፣ የጥበብ ሥራዎቻቸውን የሚጋሩበት ሰፊ መድረክ የለም" በማለት ተቋማዊና የሙያ አጋርነት ተግዳሮችን ነቅሶ ያመላክታል።

ለሰዓሊ ወርቅነህ 'ሥነ ጥበብ የሕብረተሰብ ምሰሶ ነው'።



Share