የሜልበርን ዋንጫ፤ አውስትራሊያን ሰቅዞና አለያይቶ የሚይዘው የፈረስ ውድድር

Melbourne Cup

Source: AAP

የሜልበርን ዋንጫ የአውስትራሊያ እጅጉን ዝነኛ የፈረስ ውድድር ትዕይንት ነው። አያሌ ታዳሚዎችን የማማለል ታሪክ እንዳለው ሁሉ፤ የውድድር ኢንዱስትሪውን ሥነ ምግባራትና ትግበራዎችን፣ የእንሰሳት አያያዝና የቁማር ችግር ፈጣሪነት አስመልክቶ ብርቱ ጥያቄዎችንም ይቀሰቅሳል።


አንኳሮች
  • የዋንጫ ቀን ሜልበርን ውስጥ ሕዝባዊ በዓል ነው፤ የሚውለውም በየዓመቱ ወርኃ ኖቬምበር በገባ የመጀመሪያው ዕለተ ማክሰኞ ላይ ነው።
  • የሜልበርን ዋንጫ በባሕል የበለፀገ ግና የተፃረሩ ሕዝባዊ አተያዮችን የተላበሰ ነው።
  • ዋንጫው ከፈረስ ውድድር ጋር ተያይዞ የእንሰሳት ሥነ ምግባራትና ደኅንነትን አስመልክቶ እየናሩ ያሉ ትችቶች እየገጠሙት ነው።
  • የዋንጫ ቀን በእጅጉ አስደማሚ የአንድ ቀን የቁመራ ኩነትም ነው።
በኖቬምበር የመጀመሪያው ዕለተ ማክሰኞ ድፍን አውስትራሊያ የፈረስ ውድድሩን ለመመልከት የምትቆምበት ነው።

የሜልበርን ዋንጫ የአውስትራሊያ ጉልህ የፈረስ ውድድር ቀን መቁጠሪያ ሲሆን፤ ከዓለም ውስጥ አንዱ በጣሙን የተከበረ ትዕይንት ነው። ሌላው ቀርቶ በሕዝባዊ በዓልነት የተሰየመ ነው።

የቪክቶሪያ ፈረስ ውድድር ክለብ ሊቀመንበር ኒል ዊልሰን የሜልበርን ዋንጫ “እንደ እውነቱ ከሆነ የአውስትራሊያ ባሕል፣ ድርና ማግ አካል ነው”

“የዋንጫው ክንውን ቀደም ባሉት ጊዜያት የዓለም ጦርነቶችን ተቋቋሟል፣ አውስትራሊያ የምጣኔ ሃብት ድቅቀት ገጥሞት ሳለ በፅናት አልፏል፤ በቅርቡም የኮቪድ ወረርሽን ተቋቋሞ ዘልቋል” ብለዋል።

ዊልሰን የሜልበርን ዋንጫ ከ162 ዓመታት በላይ ባስቆጠረ የውድድር ዘመን ዕድገቱ እንደ ግራንድ ፕሪክስ ወይም ቴኒስን ከመሰሉ ዋነኛ ዓለም አቀፍ ስፖርቶች ጋር በንፅፅር ለመታየት መብቃቱን አንስተዋል።

አያይዘውም “በ160 አገራት 750 ሚሊየን የሚደርሱ ታዳሚዎች አሉን” ብለዋል።

በአንድ ወገን በርካታ አውስትራሊያውያን በዕለተ ዋንጫው በሐሴት ሲያሳልፉ ሌሎች አበክረው ያወግዙታል።
SG MELBOURNE CUP racegoers
Racegoers cheering during Melbourne Cup Day, at Flemington Racecourse. Source: AAP / JAMES ROSS/AAPIMAGE
የውድድር ፈረሶች ደኅንነት ጥበቃ ቅንጅት ዳይሬክተር ክሪስቲን ሊኽ፤ ከአንድ አሠርተ ዓመት በላይ ድርጅታቸው "እምቢኝ ለዋንጫው" በሚል የተቃውሞ ድምፁን ሲያሰማ ቆይቷል።

ሊኽ የፈረስ ውድድሩ ለገንዘብ ትርፍ ሲል በእንሰሳቱ ላይ የሚያሳድራቸው ተፅዕኖ ጥያቄዎች ሊቀርቡባቸው እንደሚገባ ይናገራሉ።
የሜልበር ዋንጫ በአብዛኛው የሚታየው በጋራ አንድ ላይ ተገኛኝተን የምናከብረው ዕለት ተደረጎ ነው፤ አከባበራችን ግና የተሳሳተ ነው።
ክሪስቲን ሊኽ፤ የውድድር ፈርሶች ደኅንነት ቅንጅት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር
RACING MELBOURNE CUP PROTESTS
Animal rights activists regularly protest Melbourne Cup Day. Source: AAP / SCOTT BARBOUR/AAPIMAGE

የሜልበርን ዋንጫ ፋይዳ ምንድነው?

የሜልበርን ዋንጫ በፍሌሚንግተኑ ውድድር ሰባተኛው የዋንጫ ፉክክር ነው። የሜልበርን ዋንጫ ለአንድ ሳምንት የሚዘልቀው የዋንጫውና የፀደይ የፈረስ ውድድር ካርኒቫል ፈርጥ ነው።

እናም ኖቬምበር በገባ የመጀመሪያው ማክሰኞ 3 pm ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የውድድሩ ታዳሚዎች በያሉበት ሆነው ዓይኖቻቸውን ሳይነቅሉ የፈረስ ውድድሩን ይከታተላሉ።

“ለዚያም ነው 'አገርን ቀጥ አድርጎ የሚያቆም ውድድር' ተብሎ የሚጠራው" ሲሉ ወ/ሮ ዊልሰን ይናገራሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ከሁለት አዋቂ ሰዎች አንዳቸው ውድድሩን ለማድመጥ ወይም ለመመልከት በያሉበት ይፀናሉ።
ኒል ዊልሰን፤ የቪክቶሪያ ፈረስ ውድድር ሊቀመበር
በዋንጫው ውድድር ዕለት 300,000 ያህል ሰዎች በፍሌሚንግተን የመወዳደሪያ እመም ዙሪያ ኩነቱን በሕብረቀለማት አድምቀው ይውላሉ።

ዊልሰን “ፋሽን የኩነቱ አንዱ ትልቅ አካል ነው፤ ሰዎች ባርኔጣቸውን ደፍተው፣ በኮትና ሱሪ ተሽሞንሙነውና በአጌጡ ቀሚሶች ተውበው ለመገኘት ጓጉተው ይጠብቃሉ” ሲሉ ይገልጣሉ።
SG MELBOURNE CUP Quantico
Jockey Kerrin McEvoy (left) rides Quantico to victory in race 10, MSS Security Sprint during Melbourne Cup Day, at Flemington Racecourse, Melbourne, Tuesday, November 2, 2021. Source: AAP / JAMES ROSS/AAPIMAGE

የዋንጫ ሽልማት ዶላርና ቁማር

የሜልበርን ዋንጫ ከዓለም የከበርቴ ውድድሮች አንዱ ነው። በ2022 $8 ሚሊየን የሚያስገኝ ሲሆን፤ አሸናፊው $4 ሚሊየንና $250,000 የሚያወጣ ዋንጫ ይሸለማል።

የዋንጫው ቀን በሌላም በኩል የአውስትራሊያ ትልቁ የአንድ ቀን የቁማር ኩነት ነው። በዓመት አንዴ ቁማር መቆመር የሚሹ ይቆምራሉ፤ መሥሪያ ቤቶች ውስጥም በአብዛኛው ዕጣ መሰል ቁመራ ይካሔዳል።

የውድድር ፈረሶች ደኅንነት ቅንጅት የሜልበርን ዋንጫ በቆማሪዎች ኪሳራ ለቪክቶሪያ ምጣኔ ሃብት ደጓሚ መሆኑን ያመላክታል። ቁማር አውስትራሊያ ውስጥ አንዱ አዋኪ ጉዳይ ሆኖ አለ።

ወ/ሮ ሊኽ “ባለፉት 10 ዓመታት የውርርድ መጠን አሻቅቧል። በየዓመቱ የሚካሔደው የፈረስ ውርርድ ቁመራ አሁን $29 ቢሊየን ደርሷል። እናም፤ የፈርስ ውድድር መጥፎነቱ ለፈረሶች ብቻ ሳይሆን ለሰዎችም ጭምር ነው" በማለት ተናግረዋል።

ሰዎች የሚቃወሙት ለምንድን ነው?

ለዓመታት የፈረስ ውድድር ኢንዱስትሪ የእንሰሳት ደኅንነትን፣ የእርባታ ሂደትንና ጭካኔ የተመላበት ስልጠናን አስመልክቶ ብርቱ ምርመራ እየደረሰበት ነው።

እንዲሁም፤ እሽቅድድምና የገረፋ ቴክኒኮች ተፅዕኖዎች ሳቢያ የቆሰሉ ፈረሶችን ለሞት የማብቃቱ አስባብ አሳድሯቸው ያሉ የሥነ ምግባር ጥያቄዎች አሉ።

ወ/ሮ ሊኽ ይህን ሲብራርሉ “ባለፉት 10 ዓመታት በደረሰባቸው ቁስሎች ሳቢያ ስምንት ፈረሶች በፍሌሚንግተኑ የሜልበርን ዋንጫ ዕለት እንዲገደሉ ተደርገዋል” ባይ ናቸው።
ስለምን፤ መልሶ ማገገም ውድ፣ ጊዜ ወሳጅና ለአንድ ፈረስ በጣሙን አዋኪ በመሆኑ እዚያው በተወዳደሩበት እመም ዙሪያ ይገድሏቸዋል።
ወ/ሮ ሊኽ በፈረስ እሽቅድድም ሳቢያ ያለውን የሞት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ሕዝብ ሙሉዕ ግንዛቤ እንደሌለው ሲያመላክቱም፤

“አንድ ፈረስ በአውስትራሊያ የውድድር እመም ላይ በአማካይ በየ2.5 ቀናት ይሞታል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ከቆሰሉባቸው የመወዳደሪያ ሥፍራዎች ገለል ተደርገው ይገደላሉ። ስለ እነሱም የምናውቀው ነገር የለም" ብለዋል።

ይሁንና ዊልሰን በዋንጫው ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችንና ትኩረቱ እየበረታ የመጣውን የእንሰሳት ደኅንነት አስመልክተው የሚሰነዘሩ ትችቶችን ይከላከላሉ።

“ሰዎች በሚያመሰግኑበት ደረጃም ባይሆንም ለፈረሶቹ የሚደረጉ ክብካቤዎች ከፍ እያሉ መጥተዋል”

“በአቅራቢያቸው የእንሰሳት ሐኪም አለ፤ የጥርስና የአጥንት ክብካቤም አላቸው። በጣሙን ስንዱ ናቸው።”
MELBOURNE CUP PROTEST
Animal activists stage protests with mock fashion and fake races during Melbourne Cup Day. Source: AAP / DAVID CROSLING/AAPIMAGE
የቪክቶሪያ የእንሰሳት ሕክምና አገልግሎ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ግሬስ ፎርብስ፤ የሕክምና ቡድናቸው የመቁሰል አደጋ መጠንን ለመቀነስ ማለፊያ የእንሰሳት ሕክምና ፕሮቶኮሎችን ያበጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ በሉላዊ ደረጃ ምርጥ የሆነ የፈረስ እሽቅድድም የደኅንነት ሬኮርድ ያለን ቢሆንም፤ ከዚያም የላቀ ለማድረግ ከመሞከር ምንም የሚገታን የለም።
ዶ/ር ግሬስ ፎርብስ፤ የፈርስ ውድድር ቪክቶሪያ የእንሰሳት ሕክምና አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የቪክቶሪያ ውድድርና የቪክቶሪያ መንግሥት ፈረሶቹ ለፀደይ ካርኒቫል ውድድር ከመቅረባቸው በፊት የአካል ጉዳት መጠን የሚቃኝ እጅግ ዘመናይ የተሰኘ ሙሉ የውስጥ ሰውነት መመልከቻ የሕክምና መሳሪያ በጋራ ገዝተዋል።

ይህንንም አስመልክቶ ዶ/ር ፎርብስ ሲናገሩ “በእዚህ አዲስ መሳሪያ ነቅተውና ቆመው ሳሉ በጣሙን ዝርዝር የሆኑ የውስጥ ሰውነት ምልከታዎችን ማድረግ እንችላለን” ብለዋል።
Melbourne Cup winner Stakes Day
Thoroughbreds are a type of horse breed known for their fast running speed. They can maintain speeds between 60 to 70 km/hr. Source: Getty / Getty Images AsiaPac

የትኞቹ ፈረሶች ናቸው መወዳደር የሚችሉት?

ለ3200 ሜትሮች ውድድር ተፎካካሪ ሆነው የሚቀርቡት 24 ለእሽቅድድም ብቁ የሆኑ የውድድር ፈርሶች ናቸው። ፈርሶቹ ቢያንስ የሶስት ዓመት ዕድሜ የሞላቸውና ጥብቅ የሰውነት ክብደት መመዘኛን ያሟሉ መሆን ይገባቸዋል።

የሜልበርን ዋንጫ 'አዋኪ' እሽቅድድም ነው። ፈረሶች እንደ ዕድሜ፣ ክብደትና ቀደም ያለ የውድድር ውጤታቸው መሠረት ተጨማሪ ጫና አለባቸው። በዚህ መልኩ እያንዳንዱ ፈረስ እኩል የአሸናፊነት ዕድል አለው።

በጣሙን ዝነኛ የሜልበርን ዋንጫ አሸናፊ ፈረስ የ1930ው ፋር ላፕ ነው። ውርሰ አሻራውን ለማቆየት በሜልበር ሙዚየም ይገኛል። ልቡ ካንብራ ተጠብቆ አለ።
HELP FOR GAMBLING ADDICTION
English_Settlementguide_19082022_Gambling.mp3 image

Getting help when your loved one has gambling problems

SBS English

19/08/202208:34

Share