ስጦታው በፍቃዱ፤ ከማይጨው እስከ አውስትራሊያ

Setotaw Befekadu Author.jpg

Author Setotaw Befekadu. Credit: S.Befekadu

"ከማይጨው እስከ ሲድኒ" ግለ ታሪክነቱ የደራሲ ስጦታው በፍቃዱ ቢሆንም፤ የተነሳሽነት ግፊትና ዕሳቤዎቹ የፈለቁት ግና ከአንድ የእምነት ተጋሪ ወዳጃቸውና ከሴት ልጃቸው ሊዲያ ነው።


የወዳጃቸው ዳዊት ዕሳቤ የእሳቸው ታሪክ 'አስተምህሮቱ የጥቂት ሰዎችንም ሕይወት እንኳ ቢሆን ሊለውጥ ይችላል' ከሚል ነው።

የሴት ልጃቸው ሊዲያ ግፊት ስለ አባትዋ ቤተሰቦችና የአስተዳደግ ታሪክ በጥልቀት ለመረዳትና ቤተሰባዊ ምንጯን ለመረዳት ካለ ጉጉት ነበር።

አቶ ስጦታው የወዳጅና ሴት ልጃቸውን ምክር አሰላስለው ከውሳኔ ላይ ደረሱ።

የውልደትና ሠፈራ ከተሞችን ስም አዋድደው "ከማይጨው እስከ ሲድኒ... ያ ሰው እኔ ነኝ፤ እግዚብአሔር ይክበር" መፅሐፋቸውን ለአንባቢያን በረከት ይሆን ዘንድ እነሆኝ ለማለት በቁ።

ከማይጨው አጭር የለጋ ወጣትነት ሕይወት በኋላ፤ ከቤተሰብ ጠፍተው በአላማጣ በኩል በእግር ደሴ ገቡ። አዲስ አበባ በመኪና ተጉዘው ዘለቁ።

አዲስ አበባ አዋዝታ ወጣቱን ስጦታውን በአማላይ የምሽት ሕይወትና ሱስ አጠመደች።

ከትምህርት ቤት ይልቅ የሲጋራ ሱስና የምሽት ዳንኪራ ቤቶች ቅድሚያን ያዙ።

ተደባዳቢነት ገነን የሠፈር መለያ ሆነ።

አንድ ቀን 'ከሰማይ ገንዘብ እናወርዳለን፤ በሽተኞችን እንፈውሳለን" የሚሉ አሉ ሲባል ሰምተው 'ይህን ጉድ' ልይ ብለው ተነሱ።

እግሮቻቸው የፀሎት ቤት ደጃፍን ተሻግረው ገቡ።

ለዳንኪራ ቤቶችና ድብድብ ጀርባቸውን ሰጡ።

የሕይወት ኮከባቸው ተለወጠ።

ቀስቱን ወደ አገረ አውስትራሊያ አመለከተ።








Share