ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው፤ ከጎንደር እስከ አውስትራሊያ

Dr Tesfaye Yigzawe pic I.png

Dr Tesfaye Yigzawe. Credit: SBS Amharic

ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው የወቅቱ በቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ፕሬዚደንት ናቸው። ከውልደት ሥፍራቸው ጎንደር ከተማ እንደምን ለሀገረ አውስትራሊያ እንደበቁ ግለ ታሪካቸውን አጣቅሰው ያወጋሉ።


ውልደትና ዕድገት

የዶ/ር ተስፋዬ ዕትብት ተቆርጦ የተቀበረው በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነገሥታቱ ዙፋን ረግቶ ለመዲናነት በበቃችውና የአልጋ አርጊው አፄ ፋሲል የንግሥ ከተማ በሆነችው ጎንደር ነው።

የፋሲል ግንብ ዕድሜ ጠገብ ቢሆንም ግርማ ሞገሱ ሁሌም ለዓይን አዲስ፤ ዘመናትን ቢያሸመግልም ታሪኩ ጆሮ ገብ የኢትዮጵያዊነት ዋቤና ምሰሶ ሆኖ አለ።

የቱሪዝም መስህብነቱ ምስጢር፤ የዓለም ቅርስነት ፋይዳውም ባሕር መዝገብ ላይ ሠፍሮ ያለው ለእዚያ ነው።

በዘመነ የማንነት ቀውስ የተስፋዬ የኢትዮጵያዊነት ፅናት ምንጭም እሱ ነው።
Gondar.png
Kings Town, Gonder Ethiopia. Credit: Sepp Puchinger
ዶ/ር ተስፋዬ በ "44ቱ" ታቦት ከተማ ብቻቸውን ተወልደው አላደጉም።

ለወላጆቻቸው ከሶስት ወንዶች ልጆቻቸው መካከል ሁለተኛው ናቸው።

ፊደል ቆጥረው፤ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የቀለም ትምህርታቸውንም ያጠናቀቁት እዚያው ጎንደር ከተማ ነው።

ዩኒቨርሲቲ እስከገቡ ድረስ ከጎንደር ወጥተው አያውቁም።

ከወንድሞቻቸውና እናታቸው ጋር እዚያው ቆይተዋል።

እናታቸው መምህርት ንግሥት በላይ የእናትነት ግብራቸው ሞገስ ይሁንላቸውና የእነ ተስፋዬ አሳዳጊ ብቻም አልነበሩም።
Nigist Belay.png
Dr Tesfaye Yigzawe with his mother, Nigest Belay. Credit: T.Yigzaw

ሌሎችም ልጆችንም ታድገዋል። የሕይወት አቅጣጫም መርተዋል።

የዶ/ር ተስፋዬ የወጣትነት ዘመን በቀኃ ወንዝ ዋና ብቻ ውስን አልነበረም።

እግር ኳስ ተጫውተዋል፤ መዘዞ ቁመታቸውን ለቅርጫት ኳስ ጨዋታ ተጠቅመውበታል።

የትምህርት ሕይወት ጥሪ ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እስከመራቻቸው ድረስ።

የዩኒቨርሲቲ ሕይወት - መማርና ማስተማር

ዲላ ከተማ እጆቿን ዘርግታ ተቀበለቻቸው። ዕቅፏ ውስጥ አስገባቻቸው።
ዲላም እንደ ጎንደር ሀገሬ ነው።
ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው
ዲላ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ሰጣቸው።
Gradtuation.png
Graduation. Credit: T.Yigzawe
የላቀ ውጤት አምጥተው ነበርና የዩኒቨርሲቲው የፊዚክስ መምህርም አድርጎ አሠማራቸው።

የመምህርት ልጅ መምህር ሆኑ።

እምብዛም ሳይቆዩ ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ጥናት ከዲላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘለቁ።

ተመረቁ።

የፊዚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ ዲላ ተመለሱ።

ቀደም ሲል መምህርነትን እምቢኝ ብለው አንገራግረው የነበሩት ተስፋዬ በውስጡ ሲያልፉ የመምህርነትን የልሕቀት ደረጃ ልብ አሉ።

ዛሬም ድረስ ውስጣቸው አለ።
በሕይወት ዘመኔ ተመልሼ መሥራት የምፈልገው ሥራ መምህርነት ነው፤ የሥራ እርካታ አለው።
ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው
በዲላ መምህርነትና በሁለተኛ ዲግሪ ክህሎት መወሰን ያልፈልጉት ተስፋዬ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመለሱ።

ለሶስተኛ ዲግሪያቸው እየተማሩና እያስተማሩ ሳለም የነፃ ትምህርት ዕድሎችን ማፈላለግ ያዙ።

አውስትራሊያና አውሮፓ የዩኒቨርሲቲ በሮቻቸውን ከፈቱላቸው።

ዝነኛው የአውስትራሊያ መታወቂያ ፊልም "Crocodile Dundee" አዕምሯቸው ውስጥ ተመላለሰ።
Crocodile Dundee.png
Paul Hogan carrying a dead crocodile in a bar in a scene from the film 'Crocodile Dundee', 1986. Credit: Paramount/Getty Images
የፊልሙን ገፅታ በዓይናቸው ለማየት ወደዱ።

አውስትራሊያን መረጡ።

ሜልበርን ስዊንበርን ዩኒቨርሲቲ ገቡ።

በመጀመሪያው ሳምንት የዩኒቨርሲቲውን ገጠራማ ዙሪያ ገባ ሲመለከቱ አውስትራሊያ ስለመኖራቸው ተጠራጠሩ።

አውሮፕላኑ መልሶ ያሳረፋቸው ጎንደር እስኪመስላቸው ድረስ ጥርጣሬ ገባቸው።

የሚያውቁት ሰው በዙሪያቸው አልነበረምና ብቸኝነት አጠቃቸው። ተመልሰው ወደ ሀገር ቤት መሔድ እስኪመኙ ድረስ።

ሆኖም፤ ለመዱት። ተወጡት።

በፊዚክስ የሶሶተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተው ተመረቁ።
Tesfaye Yigzawe PhD.png
Tesfaye Yigzawe, PhD graduate picture at Swinburne University of Technology. Credit: T.Yigzaw
ከምረቃቸው በፊት በብቸኝነት በመከፋት ወደ ሀገር ቤት መመለስ የሻቱትን ያህል፤ ከምረቃ በኋላ አውስትራሊያ መቅረትን ወደዱ።

አውስትራሊያ ኢትዮጵያዊት-አውስትራሊያዊት ሴት ልጇን እነሆኝ አለቻቸው።

ተቀበሉ። ተፋቀሩ። ተጋቡ።
TY Family pic .png
Dr Tesfaye Yigzawe with his daughter Meklit Yigzawe (C) and his wife Genet. Credit: T.Yigzzaw
ለአንዲት ሴት ልጅ አባትነትም በቁ።

ከፊዚክሱ ዓለም ተነጥለው ወደ ባንክ ሠራተኛነት ዞረዋል።

ለወደፊቱም በባንኩ መስክ ለመቀጠል ዕሳቤ አላቸው።

ወደ መምህርነት የመመለሱ ትልም እንዳለ ሆኖ።

የዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው ግለ ታሪክ ወግ በእዚሁ አልተቋጨም።

በቀጣዩ ክፍለ ዝግጅታችን እንደምን ከአውስትራሊያ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ጋር እንደተቀላቀሉ፣ የቤተሰብ ምሥረታና የወደፊት ውጥኖቻቸውን አንስተው ያጋራሉ።





Share