"በኢትዮጵያዊነታችን እናምናለን የምንል ከሆነ፤ የግል የፖለቲካ አቋማችንና ሃይማኖታችንን ሳናንፀባርቅ ወደ አንድነት እንምጣ" ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው

Dr Tesfaye Yigzawe II.png

Dr Tesfaye Yigzawe, President of the Ethiopian Community Association of Victoria. Credit: SBS Amharic

ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው፤ በቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ፕሬዚደንት፤ ለማኅበረሰብ አገልጋይነት ገፊና ሳቢ የሆኗቸውን አስባቦች፤ በቀዳሚው ክፍለ ዝግጅታችን ያወጉት 'ከጎንደር እስከ አውስትራሊያ' ግለ ታሪካቸው ተከታይ አድርገው ይናገራሉ።


ከማኅበረሰብ ጋር መቀላቀል

በነፃ ትምህርት ዕድል የመጡት ተስፋዬ ይግዛው፤ በሜልበርን የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪነታቸው ወቅት እንደ ዩኒቨርሲቲያቸው ከከተማ ፈንጠር የማለት ያህል በእንግድነታቸው ሳቢያ ከማኅበረሰቡ የራቁ ነበሩ።

ሆኖም ግና የአሁኗን ባለቤታቸውንና የሴት ልጃቸው መክሊትን እናት የመተዋወቅ ያህል ርቀት ያሉ ባይተዋር አልነበሩም።

ለግለ ሕይወት የስኬት ሚዛን ጭምር ሆነዋቸዋል።
ባለቤቴና ልጄ ለእኔ ትልቁ ዕሴቶቼ ናቸው።
ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው
ምኞትና ፀሎት

ዶ/ር ተስፋዬ በባንክ ሙያቸው የተጋላጭነት ትንታኔ ላይ የማተኮራቸውን ያህል ስለ ነገ ሲያስቡ በእራሳችው ዙሪያ ብቻ ውስን አይደለም።

ባሕር ተሻግሮ መተኪያ የሌላት የውድ ሃገራቸው ኢትዮጵያ መፃኢ ዕጣ ፈንታ ያስጨንቃቸዋል፤ እንደ ሁለት ባለ ሀገርነታቸው የአውስትራሊያ ጉዳይ ያሳስባቸዋል፤ ሲልም እንደ ዓለም ማኅበረሰብ አካልነታቸው ሉላዊ ስጋት ይታሰባቸዋል።
ደረታችንን አሳብጠን ከእኔ በላይ ማንም የለም የሚለውን ትተን በተቻለ መጠን ችግሮቻችንን ብንፈታ ጥሩ ነው። የሁሌም ፀሎትና ምኞቴ ሰላም ነው። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ተቻችለው እንደኖሩት ደም የማይፈስባት ሀገር እንድትኖረን ነው።
ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው
ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶችና ጥሪዎች

ዶ/ር ተስፋዬን ለማኅበረሰብ የበጎ አድራጎት አገልግሎት አነሳስቶ በቪክቶሪያ ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ፕሬዚደንት ያደረሳቸው የተማሪነት ጊዜ ባይተዋርነትና ብቸኝነት ተሞክሯቸው አንኳር ተጠቃሾች ናቸው።

ሌሎች የማኅበረሰብ አባላትም እሳቸው ባለፉበት ኮምጣጣ የሕይወት ጉዞ ውስጥ እንዳያልፉ ይሻሉ።

ዕሳቤያቸው ለአዲስ ፍልሰተኞች ብቻም ሳይሆን በርካታ አሠርት ዓመታትን በሀገረ አውስትራሊያ ያሳለፉ ጎልማሶችና ተወላጆችንም ያክላል።
አብረን ከቆምን ብዙ ነገሮችን እንቀይራለን።
ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው
በፖለቲካ፣ በሃይማኖትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ከማኅበረሰቡ የጋራ እንቅስቃሴዎች ተነጥለው ላሉ ግለሰቦችና ቡድኖች የእንሰባሰብ የአንድነት ጥሪም ያቀርባሉ።
በኢትዮጵያዊነታችን እናምናለን የምንል ከሆነ፤ የፖለቲካ አቋማችንና ሃይማኖታችንን ሳናንፀባርቅ ወደ አንድነት እንምጣ።
ዶ/ር ተስፋዬ ይግዛው

Share