አንኳሮች
- የነባር ዜጎች ባሕላዊ እሳት ልኮሳ ትግበራ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የደን ቃጠሎ መቀነሻና የሀገር ጤናን ማስተዋወቂያ "የተፈተነ" ወደ ፊት መራመጃ መንገድ ነው
- የአውስትራሊያ ነባር ዜጎችን የመሬትና ውኃ ባለቤትነት መብቶችን የሚያጎናፅፈው የጋራ ብልፅግናው ሕግ ባሕላዊ እሳት ልኮሳን በሚያውቁበት ብልሃት ተጠቅመው ትድግናን እንዲያገኙ ይሁንታን የሚቸር ሲሆን፤ ውጤታማ ስለመሆኑም መረጃዎች ያመላክታሉ
- ባሕላዊ እሳት ልኮሳን ግብር ላይ ማዋል የደን ቃጠሎ ቅነሳን አካትቶ ሌሎችም ታካይ ፋይዳዎች አሉት
ብዙዎቻችን አውስትራሊያ ውስጥ አግባብ ባለው መልኩ የ2019–20 የጥቁር በጋንና እንዲሁም በቅርቡ መጠነ ሰፊና ብርቱ የደን ቃጠሎ የነበረውን የ2024 የከፋ ጉዳት ስናስብ እሳትን የምንመለከተው በእጅጉ አስጊ ስለመሆኑ ነው።
ይሁንና፤ በነባር ዜጎች ዘንድ እሳት የደን ቃጠሎን አክሎ፤ መሬትን በተገቢ መልኩ ለመጠቀም፣ ዕቅድን ለዘለቄታ ለማብቃትና ሥነ ምሕዳርን ለመታደግ አስፈላጊ ነበር።

Wunambal Gaambera Aboriginal Corporation chair Catherine Goonack is among those holding the baton of the fire tradition in Australia today. She learnt cultural burning directly from her ancestors. Photo: Russell Ord for WGAC
“አባቴ፤ ሰብልን ለማብቀል በየዓመቱ ማቃጠል እንደሚኖርብን ይነግረን ነበር"
“ባሕላዊ ቃጠሎ የቀደምቶቻችን መንገድ፣ የሕይወት ዘዬ ነው። በአገር ላይ ዳግም ነፍስን ለመዝራት፣ ዕድገትን ለማስገኘትና የደን ቃጠሎን ከመከሰት ለመግታት እሳትን ይጠቀሙ ነበር ” ሲሉ የዉናምባን ጋምቤራ ነባር ዜጎች ኮርፖሬሽን ሊቀመንበር፤ ካትሪን ጉናክ ይናገራሉ።
ይህ ባሕላዊ ቃጠሎ በሚል የሚታወቀው ልማዳዊ ተግባር ከቅኝ ግዛት አንስቶ በስፋት ግብር ላይ አልዋለም።
ወ/ሮ ጉናክ “አረጋውያኑ የምድሪቱን ጤና ለመጠበቅ ቃጠሎ ማካሔድ ጠቃሚ እንደሁ ያውቃሉ" ሲሉም ያስረዳሉ።
በ 2024 በተባባሪ ፀሐፊነት ለሕትመት ባበቁት በምዕራብ አውስትራሊያ ሩቃማ ሰሜናዊ ኪምበርሊ መጠነ ሰፊ ልማዳዊ የእሳት ቃጠሎ ግብር ላይ በመዋሉ ሳቢያ ምን ያህል የእሳት ሁኔታዎች እንደተሻሻሉ ሰንደዋል።
“የደን ቃጠሎዎችን ለመከላከል እንዲያስችል ላለፉት 10 ዓመታት የቅርብ ክትትል አድርገናል። ሽቅብና ቁልቁል ማለት ገጥሞናል፤ ይሁንና አሁን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ተመልሰናል” ብለዋል።
ጥናቱ አራት ልማዳዊ ባለቤት ቡድኖች ቀደም ሲል የሳቫና ምድረ ገጽ አካባቢ በእጅጉ ተፅዕኖ የነበረው ብርቱ የደን ቃጠሎን እንደምን ቅድመ መከላከል ለማድረግ እንደበቁ መዝኗል።

Skills of assessing the right timing, and how to burn the right way, survive to this day. Fire walk by Jeremy Kowan, Uunguu Ranger and Wunambal Gaambera Traditional Owner. Photo: Mark Jones for WGAC
ባሕላዊ ቃጠሎ መሥራቱ ከተረጋገጠ፤ ስለምን ነው ዳግም ግብር ላይ እንዲውል የማይደረገው?
የመሬት ባለቤትነት ለልማዳዊ ባለቤቶች መመለስን ተከትሎ፤ አውስትራሊያ ውስጥ ከሌሎች መደበኛ ዘዴዎች ጋር ታክሎ ባሕላዊ ቃጠሎ ፕሮግራም ግብር ላይ ለመዋል በቅቷል።
የጥናቱ ዋነኛ ፀሐፊ ቶም ቪጂሊያንቴ የልማዳዊ ባለቤትነት መብቶች መገኘት "ወሳኝ ወቅት ነበር" ብለዋል።
“ስለምን፤ ያኔ ሰዎች መሬታቸውን እንዳሹ የማስተዳደር መብቶች ነበሯቸው።"
“ሌላው ቃጠሎ የማካሔጃ አማራጭ በብሔራዊ ፓርኮች ወይም የመንግሥት ኤጄንሲዎች ኃላፊነት ስር ያለ መሬት ነው።እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች፤ ነባር ዜጎች ቃጠሎን ለማካሔድና ተፅዕኖን ለማሳደር ይጥራሉ፤ ሆኖም እንዳሻቸው የመፈፀም መብት የላቸውም" ይላሉ።
ትሬቨር ሐዋርድ፤ በአውስትራሊያ እሳትና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ባለስልጣናት ምክር ቤት የብሔራዊ የተፈቀደ ቃጠሎ አገር አቀፍ ሥር አስኪያጅ ናቸው።
በኪምበርሊ እና ሳቫና ቀጣና ዙሪያ ገባ የእሳት አያያዝን እንደ “በተቀረውም የአውስትራሊያ ክፍሎች ስኬታማ ሊሆን የሚችል ጥሩ ተምሳሌ" አድርገው ይመለከታሉ።
“የእዚያ አካባቢ ገጸ ምድር ባለፉት 20 ዓመታት በእጅጉ ተለውጧል።
“በእጅጉ ብርቱና መጠነ ሰፊ የነበሩ የደን ቃጠሎዎች ነበሩት፤ አሁን ግና በጣሙን በተሻለ መልኩ ይመራል፤ እንዲሁም አነስተኛ ግለትና ተገቢ በሆነ ዓመታዊው ወቅት በቂ ቁጥጥር ባለበት ሁኔታ በሳይንስ ፕሮግራምነት በነባር ዜጎች መሪነት ይካሔዳል" በማለት ይገልጣሉ።

Mr Vigilante elaborates on fire management techniques in North Kimberley: “A lot of burning is done by vehicles, some walking in the bush or burning around cultural sites. We also use aircraft because we're looking after close to a million hectares.” Photo: WGAC
ከእዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑቱ ምን ያህሉ ክፍለ አገራትና ግዛቶች ናቸው ለሚለው፤ ከልማዳዊው ባለቤቶች ጋር የሚወሰን ይሆናል። .
“ስለምን፤ አውስትራሊያ ውስጥ በርካታ የነባር ዜጎች ቡድናት አሉን፤ እናም እያንዳንዳቸው እኒህ ቡድናት ከምድሪቱ ጋር የየእራሳቸው ትስስሮሽ አላቸው።
“እናም፤ ስለ እውነት የእያንዳንዱን የክፍለ አገራትና ግዛት ኤጄንሲዎች የእኒህን ቡድናት መንፈሳዊ መነቃቃት አስባብና ፍላጎቶች ለመረዳትና ባሕላዊ ቃጠሎ ትግበራዎችን በእራሳቸው መንገዶች፤ በእራሳቸው መሬት ላይ እንዲከውኑ ለማገዝ አብረዋቸው ሊሠሩ ይገባል” ይላሉ።
እሳት እንደምን የነባር ዜጎች መሬት ጤናን እንደሚታደግ
ጋሬዝ ካት የነባር ዜጎች የበረሃ ሽርካ ሥራ አስኪያጅ ናቸው።
ከ2012 አንስቶም በሰሜናዊ ግዛት፣ ምዕራብ አውስትራሊያና ደቡብ አውስትራሊያ ለነባር ዜጎች የተፈጥሮ ጥበቃና ተከባኪ ሆነው ሠርተዋል።
አብዛኛው የሥራቸው አትኩሮት የነበረውም ባሕላዊ ቃጠሎን በዘመናዊ መንገድ ግብራዊ መጠኑን አዛንቆ ማዋደድ ላይ ነው።
የደን ቃጠሎን የመግታት ባሕላዊ ቃጠሎ ስኬት መንስኤው የገፀ ምድር ወቅታዊ አስፈላጊነትን ተረድቶ ቅደም ተከተል በመስጠትና እንደምን ግብር ላይ መዋል እንዳለበት በሚከወን አረዳድ እንደሁ ያምናሉ።
“አብሬያቸው የምሠራቸው ሰዎች ወቅታዊ አየር ንብረትን ልብ ብለው በመመልከት፣ እሳቱ ከየት ወዴት ሊጓዝ እንደሚችል በመረዳትና ምድራቸው እንደምን ግብራዊ ምላሽ ማድረግ እንዳለባት እሳትን የሚገድቡ ናቸው” ይላሉ።
አቶ ካት የደን ቃጠሎን በመግታት ረገድ ባሕላዊ ዕውቀት ላይ የታደሰ ፍላጎት እንዳለ በማመልከት “በተለይም ከ2019-2020 ብርቱ የበጋ እሳት አንስቶ”
“ሰዎች ስለ እሳት ሲያስቡ፤ ከጀርባው ጥሎት ያለፈውን ጥቁረት፣ አብሮት የተያያዘውን አደጋ አካትተው ነው” ይላሉ።
አክለውም “ይሁንና እሳት በጥንቃቄ ምድረ ገፅ ላይ በቃጠሎ አስነሺነት ሲውል፤ አውዳሚ ኃይል ሳይሆን፤ አዳሽ ኃይል ነው የሚሆነው። እሳትን በትክክለኛ ጊዜ ገድበው ምድረ ገፅ ላይ ሳያቋርጡ ከተጠቀሙበት፤ እሳት ቅጠላ ቅጠሎች እንዲዛነቁና አዲስ ዕድገትም እንዲከሰት በጣሙን ጠቃሚ መሳሪያ ይሆናል” ብለዋል።

Joint research by members of the Ulladulla Local Aboriginal Land Council and academics from the University of Wollongong found that cultural burns significantly improve soil quality, allowing more nutrients and microbes to thrive. Photo: Paul Jones (UOW) Credit: pauljones
ፕሮፌሰር አንቶኒ ዶሲቶ፤ ይህንን ትግበራ በተመለከተ ያሉ ወቅታዊ መረጃዎችንና ውስጥ አወቅ አተያዮችን ያጋራሉ።
ጥናቱ በጥምረት የተካሔደው በዎሎንጎንግ ዩኒቨርሲቲ ተጠባቢዎችና በኡላዱላ የአካባቢ ነባር ዜጎች ምክር ቤት አባላት አማካይነት ነው።
በአፈር ላይ የሁለትዮሽ መንገዶች አዎንታዊ ተፅዕኖዎችን አሳይቷል። ይሁንና ባሕላዊ ቃጠሎ ተጨማሪ ትሩፋቶችን አስገኝቷል።
ፕሮፌሰር ዶሲቶ “ለምሳሌ ያህል፤ የአፈር ድልበትና ተፈጥሯዊነት በባሕላዊ ቃጠሎ ትልቅ ውጤት አስገኝቷል። ”
“እናም፤ ባሕላዊው ቃጠሎ ከኤጄንሲ መራሹ ቃጠሎ አካባቢ ጋር ሲነፃፀር ተጨማሪ ካርቦንና ናይትሮጂን ታይቶበታል። ካርቦንና ናይትሮጂን በእጅጉ ጠቃሚ ናቸው፤ የሥነ ምሕዳር ሥርዓት ዋነኛ ንጥረ ነገር ናቸው” በማለት ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰር ዶሴቶ መደበኛ ቃጠሎን ከባሕላዊ ቃጠሎ ጋር በአሉታዊነት ማነፃፀር እንዳልሆነም ይናገራሉ።
ይልቁንም ትኩረቱ ባሕላዊ ቃጠሎ የደን ቃጠሎን በመከላከል ረገድ የሚጫወተውን ሚና መረጃና ውስጥ አወቅ አተያዮችን መጋራት፤ እንዲሁም ነባር ዜጎች ለምዕተ ዓመታት የሥነ ምሕዳር ጤናን ከመጠበቅ አኳያ የነበራቸው ሚና ላይ እንደሆነ ያመላክታሉ።
አያይዘውም “እኒህ የማጥበቂያና ማላልሊያ መሳሪያዎች አሉን፤ የእሳት አስተዳደር ቴክኒኮች። እናም ለአሥር ሺህ ዓመታት፣ በጣሙን ለረጅም ጊዜያት ይህችን ሀገር ሲንከባከቡ የነበሩትን የነባር ዜጎች ማኅበረሰብ መሳሪያዎችን ወደ ጎን ብለናቸው ቆየን እንጂ” ብለዋል።
ስለ አዲሱ የአውስትራሊያ ሕይወትዎ ተጨማሪ ጠቃሚ መረጃና ፍንጮች ለማግኘት የአውስትራሊያ ስትገለጥ ፖድካስትን ይከተሉ አሊያም ደንበኛ ይሁኑ።
ኢሜይል ይላኩልን።