"መሬት ከፖለቲካ ወጥቶ ለኢኮኖሚው መሆን አለበት፤ አለመታደል ሆኖ የብሔር ፖለቲካ ከመሬት ጋር ተጣብቆ ተያይዟል" ዶ/ር ዳንኤል ካሳሁን

Land Reform DK.png

On June 21, 202, a farmer ploughs the land in the village of Wereb Michael, a rural area 15 km from Bahir Dar, Ethiopia, and Dr Daniel Kassahun (T-L). Credit: EDUARDO SOTERAS/AFP via Getty Images / D.Kassahun

ዶ/ር ዳንኤል ካሣሁን - በኦስተን ኮሌጅ የጂኦ ስፔስ ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ የመሬት ለአራሹ አዋጅ ግማሽ ክፍለ ዘመን መድፈን አስባብ አድርገው "የመሬት ለአራሹ አዋጅ፤ ዋዜማ፣ መባቻ፣ እና ማግሥት" በሚል ርዕስ ሰሞኑን ለሕትመት ስለአበቁት መጣጥፋቸው አንኳር ጭብጦች ያስረዳሉ።


የመሬት ለአራሹ አዋጅ፡ ዋዜማ፣ መባቻ፣ እና ማግሥት

ዳንኤል ካሳሁን

1.     መግቢያ

በየካቲት 25 1967 ዓ.ም በዓይነቱ ሥር ነቀል የሆነ “የአዋጆች ሁሉ እናት”፣ “የአክራሪ የግራ ተቃዋሚዎችን እንኳ ያስገረመ”፣ ወዘተ፣ የተሰኘና በወቅቱ የበርካቶችን ይሁንታ ያገኘ ታሪካዊ የመሬት ለአራሹ አዋጅ በደርጉ ከታወጀ፤ ዋይ ዋይ ባላባት ዋይ ዋይ ባላባት፣ እንግዲህ ቀረ ሳይሰሩ መብላት! ተብሎ ባደባባይ ከተዜመ፤ የባላባት ሥርዓቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ከሥር መሠረቱ ተመንግሎ ወደቀ ከተባለ፤ ድፍን ሃምሳ ዓመት ሞላው።

አዋጁ እንዲታወጅ ተማሪዎች ለአስር ዓመታት ተሰልፈውለት ሳለ፣ አዋጁ እንዲተገበር ወደ ስልሳ ሺህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ገጠር ዘምተውለትና ጥቂት የማይባሉት በጎጇቸው እንዳሉ በእሳት ተቃጥለውለት ሳለ፣ አዋጁ እንዳይቀለበስ ገበሬዎች፣ መምህራንና ወታደሮች ታጥቀው ከሸፈቱ የመሬት ከበርቴዎች ጋር አንገት ላንገት ተናንቀው ሕይወታቸውን ገብረውለት ሳለ፣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ መሬት መተዳደሪያው ሆኖ በአዋጁ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሥር ሆኖ ሳለ፣ የመሬት አዋጁን በተመለከተ ዛሬም በስሜት የሚያወድሱም ሆነ የሚኮንኑ ቁጠር ሥፍር የሌላቸው ዜጎችና ጸሐፍት እያሉ … የአዋጁ የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳ ባይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ጉባኤ ሳይደርግለት ፀጥ-ረጭ ብሎ “እየተከበረ” መገኘቱ እንግዳ ነገር ነው።

ለዘመናት የኢትዮጵያ ገበሬ በባላባታዊው ሥርዓት አስከፊ ሕይወት ሲገፋ መኖሩ ፀሃይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ረሃብ፣ ወረርሺኝ፣ አና ስደት ተደጋጋሚ ዕጣ ፈንታው ነበር። ይህ ማለት ሌላው የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ የደላው ነበር ማለት አይደለም።

የገበሬው አሰቃቂ ችግር እረፍት የነሳቸው የወቅቱ ተማሪዎችና ተራማጆች ብቻ ሳይሆኑ ንጉሠ ነገሥቱም ጭምር ነበሩ። ምክንያቱም ንጉሡ በዓመታዊ ፓርላማ የመክፈቻዎች ንግግር ላይ ያነሱት የነበረ ዐብይ ጉዳይ ነበርና [1]።

የኢትዮጵያ የመሬት ስሪትን ጠልቆ በመገንዘብ ሳይሆን ከቬትናም የተቀዳው የመሬት ለአራሹ መፈክር በተማሪው ተስተጋብቶ፤ “የመሬት ለአራሹን የምትሹ፤ ተዋጉለት አትሽሹ!” ወደሚል አመፅ ተሸጋግሯል። በአንድ በኩል የመሬት ጥያቄው የብሔር ጥያቄን በ1962 ዓ.ም ወልዶ የተማሪውን ተቃውሞ ሲያፈረጥም፤ በሌላ በኩል ንጉሠ ነገሥቱ የመሬት ስሪቱን አስከፊነት በመገንዘብ ከችግሩ መጠን የሚስተካከል ፈጣን እርምጃ ማከናወን ተስኗቸው ተስተውሏል።

የባላባትና የጪሰኛ ግንኙነት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ እንኳ ለፓርላማ እንዳይቀርብ በማድረጋቸው [1] ለየካቲቱ አብዮትና ለወታደራዊው አመፅ ምቹ መደላድል እንደፈጠሩ አይካድም።

የየካቲት 25, 1967 ዓ.ም የመሬት አዋጅ የኢትዮጵያውያንን ዕጣ ፈንታ በመሠረታዊነት ቢቀይረውም የመሬት ጉዳይ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ፣ የማንነት ጥያቄዎች ማጠንጠኛ ሆኖ ዛሬም ድረስ መቋጫ ያልተገኘለት የመወዛገቢያ አጀንዳ ሆኗል።

አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ መልኩን ለመመርመር ከተለያየ ዕይታ አንፃር ማየት ግድ ይላል። ይህ መጣጥፍ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ከመሬት አዋጁ ጋር የተያያዙ ስፍራዊ ጠባያት ላይ ያተኩራል።

2.    የመሬት ስሪቱ ውስብሰብ ነበር

መሬት የኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ የሕይወትና የማንነት እስትንፋስ ነው። በታሪክም ቢሆን [2] በመካከለኛው ዘመን ማብቂያ አካባቢ ኢትዮጵያውያን ሰማዩን የእግዚአብሔር መሬቱን ደግሞ የንጉሥ ነው ይሉ ነበር፤ ታዲያ ሕዝቡ እንዲህ ይል የነበረው ንጉሠ ነገሥቱን ለማሞካሸት እንጂ መንግሥት ምድራቸውን ይወስዳል ብለው አይደለም፤ ማንም ርስታቸውን ሊወስድባቸው እንደማይችል እግጠኛ ነበሩና”።

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የመሬት ስሪቱ በርካታና ውስብስብ እንደነበር ዓለምአንተ [1] በዝርዝር አቅርቦታል። የሰሜኑ መሬት የወል ሆኖ፣ የርስት/ የጉልት አገር ይባል ነበር። ማንኛውም የአካባቢው ተወላጅ አቅኚ የአባቱን ዘር ቆጥሮ የድርሻውን መሬት የማግኘት መብት ስለሚኖረው “በሺ አመቱ ይገባል ከርስቱ” ይባል ነበር። መሬቱም አይሸጥም።

ይህ የሰሜኑ ክፍል ዋንኛ ችግሩ የእርሻ መሬቱ በትውልድ ሲወራረስ እየተሸነሸነ በመበጣጠሱና ምርታማነቱ በመመናመኑ ነው። ከፍተኛ ክርክርና ሙግትም ያስከትል ነበር። በደቡብ ደግሞ መሬት የግል ሆኖ የገባር / ጪሰኛ መሬት ይባላል። ገባሩ በመሬቱ ላይ ዋስትና ስለሌለው የሚያርስበትን መሬት በባለመሬቱ እየተነጠቀ በቀላሉ ከነቤተሰቡ ሊፈናቀል የሚችል ነበር።

ሌላው ደግሞ የዘላን መሬት (የመንግሥት) ሲሆን በ1955 ዓ.ም በተደነገገ አዋጅ መንግሥት እንደፈለገው ለፈለገው ይመራውና ያድለው የነበር ነው። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) በየዓመቱ የሐምሌ 16 ልደታቸውን በማስመልከት የዘላኑን መሬት በችሮታ ለአርበኞች ያድሉ ነበር [3]።

በቅድመ አብዮት ከ70% በላይ የሚሆነው መሬት የተያዘው 1% በሆኑ ባለሀብቶች ነው ተብሎ በተለያዩ አካላት መገለፁ የሀብት ክፍፍሉን ኢ-ፍትሃዊነት ሲያሳይ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ማንኛውም ሥራ አጥና መሬት የሌለው ዜጋ ግማሽ ግማሽ ጋሻ መሬት እንዲያገኝ ንጉሡ በ1948 ዓ.ም እና በ1955 ዓ.ም ማዘዛቸው ጉዳዩን አደናጋሪ ያደርገዋል።

ለምሳሌ ራስ መስፍን ስለሺ የአንድ ጠቅላይ ግዛት ያህል ስፋት ያለው መሬት እንደነበራቸውና ልዕልት ተናኜ ወርቅ በሐረርጌ ብቻ 22 ሺህ ጋሻ መሬት ባለንብረትነት ሳይበቃቸው [3] በአብዮቱ ዋዜማ ወቅት ከአዋሽ እስከ አፍደም ቀበሌ ያለው መሬት የአያቴ የራስ መኮንን ይዞታ ስለሆነ ለኔ ይገባኛል ብለው ወደ 400,000 ሄክታር ገደማ የዘላን መሬት መጠየቃቸው [1] በወቅቱ የነበረውን ሽሚያ ማሳያ ነው።

በተጨማሪ በየካቲት 1966 ዓ.ም አብዮቱ እየተፋፋመ ሳለ ንጉሡ ለንግድ ሚኒስትሩ ከተማ ይፍሩ እና ለመከላከያ ሚኒስትሩ ጄኔራል ከበደ ገብሬ በነፍስ ወከፍ አስር ጋሻ መሬት በአርሲ በችሮታ መስጠታቸው [5] ሌላው እንቆቅልሽ ነበር።

ከለውጡ ትንሽ ቀደም ብሎ ከመቶ የሚበልጡ ዘላን የአፋር አዛውንቶች ለአቤቱታ አዲስ አበባ መጥተው ለደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ የዘላን መሬት የመንግሥት ነው ተብሎ መሬታቸንን ወስደው ጨረሱ፣ ዘራችን ሊጠፋ ነው፣ እኛም ልንጠፋ ነው ብለው ነበር [3]።

ሁሉም ገበሬ በጋራ በአስከፊ ጭቆና ሥር ይማቅቅ የነበረ ቢሆንም ከሰሜኑ ይልቅ የደቡቡ ገበሬ የበለጠ የተጎዳ ነበር። ጭሰኛው ተከራይቶ በሚያርሰው መሬት ላይ የይዞታ ዋስትና ስለሌለው ባለቤቱ በፈለገው ጊዜ በማናቸውም ምክንያት ሊያባርረው ይችላል። ምርት ሲቀንስ ተበድሮ እንዲከፍል ይደረጋል አሊያም ከርስቱ ይነቀላል።

የደቡቡ ገበሬ ተፈጥሮ የሰጠው ለም መሬቱ የበለጠ ሊጠቅመው ሲገባ በተቃራኒው የመፈናቀል ፅዋ መቅመሻ ሰበብ መሆኑ በተለምዶ እንደሚባለው የመሬቱ ለምነቱ እርግማን ሆኖበት (resource curse) ይሆን? ያስብላል።

በወቅቱ የነበረው የመሬት ስሪት ጎጂነቱ በተለያየ አካላት ተደጋግሞ ይወሳ ነበርና ሆን ብሎ ላዳመጠ በርካታ የማንቂያ ደወሎች ነበሩት።

ከዓለምአንተ [1] መረዳት እንደሚቻለው ለምሳሌ የ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ተከትሎ አልጋ ወራሽ ልዑል አስፋ ወሰን “ካሁን በኋላ ማንኛውም ሰው አስፈላጊውን መሬት ያገኛል” ብለው ለኢትዮጵያውያን አስተላልፈው ሳለ፤ በ1957 ዓ.ም ተማሪዎች መሬት ለአራሹ ብለው በአደባባይ ጠይቀው ሳለ፤ በ1958 ዓ.ም የመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስቴር ተቋቁሞ የችግሩን ግዝፈት እያሳወቀ ሳለ፤ ለጋሽ አገራት በመሬት ጉዳይ ላይ አንድ ዕልባት አድርጉ እያሉ እየወተወቱና አለበለዚያ እርዳታችንን እናቋርጣለን ብለው እያስፈራሩ ሳለ፤ ጥቅምት 23 1961 ዓ.ም ንጉሡ ለፓርማው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱ መሬት እንዲኖረው ለማድረግ ያላቸውን ርዕይ ተናገረው ሳለ፤ የመሬት ይዞታ ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ለሚንስትሮች ምክር ቤት “የባለርስትና ጭሰኛ ግንኙነት አዋጅ ባስቸኳይ በሥራ ላይ ካልዋለ ኢትዮጵያ የደም ጋን ትሆናለች” ብለው አስጠንቅቀው ሳለ፤ የዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ ምሁር ኬኔት ፓርሰንስ ለቀኃሥ የኢራን ንጉሥ መሬታቸውን ለጪሰኞቻቸው አከፋፍለው ሰጥተው ላገራቸው መፍትሔ እንዳበጁ ሁሉ ኢትዮጵያም ይህን አርአያነት እንድትከተል አበክረው ጠይቀው ሳለ፤ በርካታ የገበሬዎች አመፅ ተከስተው ሳለ…. በጭሰኛውና በባለመሬቱ መካከል ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው ውል እንዲኖር የሚያስችል መጠነኛ ማሻሻያ አዋጅ ለፓርላማ እንኳ እንዳይቀርብ አንዲት ጋት ፈቀቅ አለማለታቸው ለተጨማሪ ጥናት የሚጋብዝ ክስተት ነው።

በርካታ ምሁራን (ለምሳሌ ባሕሩ፣ ደሳለኝ) እንደሚገመግሙት የባላባት- ጪሰኛ ግንኙነት ማሻሻያ አዋጅ በሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ምናልባትም የንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣን ዕድሜም ሆነ የመሬት አዋጁ ሥር ነቀልነት ፍፁም የተለየ መልክ በያዘ ነበር።

በሌላ በኩል የሥርዓቱ ቋጠሮ ውል እንዳይጎለጎል በሚል ስጋት (Slippery Slope Argument) ሊሆን ይችላል ብሎ መከራከር ይቻላል። ለውሻ በተፈቀደ ቀዳዳ ጅብ ሊገባ እንደሚችል ሁሉ፤ ለስላሳ የተባለው የማሻሻያ አዋጅ ቢፈቀድ ውሎ አድሮ የከረረና የገዘፈ ጥያቄ አስከትሎ ለንጉሠ ነግሥቱ ሕልውና አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

ይህ ሥጋት አፍንጫዋን በርዷት የነበረችው ግመል በድንኳን ውስጥ የነበረው ግለሰብ ላይ ያደረገችውን ታሪክ ሊያስታውስ ይችላል። ሆኖም አንዳርጋቸው [4] ንጉሠ ነገሥቱ ለውጥን ባለመሻት የራሳቸውን አስከፊ ውድቀትና መቃብር ሲያዘጋጁና ሲቆፍሩ ኖሩ ብሎ ማለቱ ከንጉሡ ውሳኔ ጀርባ አንዳችም አመክንዮና እሳቤ እንዳልነበረ የሚፈርጅ ግርድፍ ትንታኔ ይመስላል።

የሚገርመው ኋላቀር እና ፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝ ተብሎ ይነቀፍ በነበረ ሥርዓት ንጉሱም ሆነ ፓርላማው ፍፁም ላይቀበሏቸው የሚችሉ አዋጆች በመንግሥት በጀት በሚተዳደር የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች - ለምሳሌ የባላባት- ጪሰኛ ግንኙነት ማሻሻያ አዋጅ - መርቀቅ መቻሉ ነው።

በተቃራኒው ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ይህን መሰል ሙከራ በደርግም ሆነ በኢሕአዴግ/ብልፅግና ዘመናት ማየት አለመቻላችን ወደኋላ የቀረነው ያኔ ወይንስ አሁን የሚል ግርምት ይፈጥራል።

3. ታሪካዊው የመሬት ለአራሹ አዋጅ

ደርግ እንደ ተማሪው ቀድሞ በፖለቲካ የነቃ አልነበረም። የመሬት ለአራሹን ጉዳይ ያነሳው የካቲት 21 ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በሄሊኮፕተር በበተነው ወረቀት ላይ ነው። ካቀረባቸው 11 ጥያቄዎች መሀል 4ኛው መሬት ለአራሹ እንዲሰጥ ነው።

ንጉሠ ነገሥቱ ገና በሥልጣን ላይ እያሉ ነበር ለመሬት ይዞታ ሚኒስትሩ ለአቶ በለጠ የመሬት አዋጅን በሚስጥር እንዲያረቁ ያዘዛቸው [5]።

ከዓለምአንተ [1] መገንዘብ እንደሚቻለው ከመሬት ይዞታ ሚኒስቴር “ተራማጅ” ምሁራን ባሻገር ኤክስፐርቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የደርጉ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ኮሚቴ ፅንፈኛ የሆነ የመሬት አዋጅ እንዲታወጅ ጫና አሳርፈዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የስዊድን እና የአሜሪካ መንግሥታት እእንዲሁም በርካታ የደርጉ አባላት ለዘብ ያለ አዋጅ እንዲታወጅ ፈልገው ነበር። ሌላው ይቅርና አዲስ አበባ የሚገኙ የሶሻሊስት አገራት አምባሳደሮች ደርጉ ያረቀቀው አዋጅ ቢታወጅ ሊያስከትል የሚችለውን ምስቅልቅል በመስጋት አዋጁ በፍጥነት እንዳይተገበር ተማጽነዋል።

“በአገራችን በሥር ነቀል የመሬት አዋጅ ሳቢያ ተከትሎ ከመጣብን ችግር ተማሩ” [6] ብለው መክረውም ነበር፤ ሰሚ አላገኙም እንጂ።

የመሬት ይዞታ ጣራውም አጨቃጫቂ ነበረ። ለደርግ የቀረበው ሐሳብ ጣራው አምስት ጋሻ ሲሆን ራሱ የሚያርስ ከሆነ አንድ ጋሻ ነበር። ደርግ “የፊዳላዊውን ሥርዓት ከናካቴው እንድናጠፋ ይረዳናል” በሚል እሳቤ [7] ጣሪያው እስከ አስር ሄክታር ብቻ ተደረገ።

አስር ሄክታር ምን ያህል ስፋት እንዳለው ለደርጉ አባላት ለማስገንዘብ በቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ችካል ተቸክሎ እንዲመለከቱት ተደርጓል [5]። በርካታ የእርሻ ባለሙያና ኢኮኖሚስት ባለበት አገር ወታደሮች የመሬት መጠንን በአይን ብቻ ተመልክተው አዋጁን እንዲያፀድቁ መደረጉ ትልቅ ስህተት ነበር።

ምናልባትም ከኢሕአፓ ጋር የነበረውን የሶሻሊስታዊነት ፉክክርን ለማሸነፍ በሩጫ አዋጁን ለማወጅ ከመሻት ይሆን?

በረቂቅ አዋጁ ላይ ድምፅ ከመስጠቱ በፊት ሻለቃ አጥናፉ አባተ የሰጡት ትንቢታዊ የሚመስል ማስገንዘቢያ ዘመኑን የቀደመ አስተያየት ነበር ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡ ይህ አዋጅ ከፀደቀ አገራችን የማትወጣው ችግር ማጥ ውስጥ ትዘፈቃለች … ባለመሬቶች ይሸፍታሉ፣ የእርሻ ሥራ ተቋርጦ የእህል እጥረት ይከሰትና ረሃብ ሊከተል ይችላል፣ ቤተ ክህነት የምትደዳረው ከመሬት በሚገኝ ጥቅም ስለሆነ ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ሊዘጉ ይችላሉ፣ ከመምዕናን ጋር ቅራኔ ውስጥ እንገባለን፣ ትርምስና ብጥብጥ በአገሪቱ ይሰፍናል፣ የኤርትራ ወንበዴዎች አጋጣሚውን ይጠቀማሉ፣ ሶማሌም ኦጋዴንን ይወራል [8] ብለው መናገራቸው ከእህል እጥረትና ረሃቡ ዘግየት ብሎ የመከሰት ጉዳይ በቀር ሁሉም ትንቢቶች ዕውን ሆነው ነበር።

የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ከተስተጋባ በአስር ዓመቱ የካቲት 25 1967 ሲታወጅ መሬት የማይሸጥ፣ የማይለወጥ፣ በወለድ አገድ የማይያዝ፣ በኪራይ መልክ ወደሌላ የማይተላለፍ ሆኖ ተደንገገ።

በተዘዋዋሪም መንግሥት ማኘክ ከሚችለው በላይ ጎረሰ። የውርሱን መብት ሙሉ ለሙሉ ባይሽረውም ማገዱ፣ መሬትን ማከራየት ከመከልከልም አልፎ በቅጥር ጉልበትን ማሳረስንም ማገዱ፣ እያንዳንዱ ባለ ይዞታ መሬቱን በራሱ ጉልበት ብቻ መጠቀም እንዳለበት መወሰኑ በርካታ አንድምታዎችን አስከትሏል፣ እስከዛሬ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

አዋጁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲታተም ብዛቱ ከመደበኛው የዕለታዊ 40,000 ኮፒ ወደ 120,000 ማደጉ [5] ህዝቡ ምን ያህል አዋጁን ለመረዳት መፈለጉን ያመላክታል።

የመሬት አዋጁ እጅግ ፅንፈኛና ሥር ነቀል ሆኖ ሳለ፣ በፍጥነት ከተደረገለት ታላቅ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ባሻገር የፖለቲካ ድርጅቶችም አድናቆታቸውን ሳይሰስቱ ችረውታል። ፋሲካ [9] የመሬት ይዞታ አዋጁ ድፍረትና ሀቀኝነት የተንፀባረቀበት እንደነበረ ገልፆ ከመሬት ባለቤቶችና ደጋፊዎቻቸው በስተቀር ሕዝቡ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ ደግፎት ነበር።

ኢሕአፓ፡ የመሬት አዋጁ ከፍተኛ ቆራጥነት የሚጠይቅ ታሪካዊ እርምጃ [10] ነው ብሎ መስክሯል፣ መኢሶን ደግሞ ኢትዮጵያ እንደዚያን ዕለት በሕዝቦቿ ደስታ ፈገግ እንደማታውቅ ... አዋጁን ማመሳከር የሚቻለው ሌኒን በ1917 ካወጀው መሬት ለአራሹ ጋር ብቻ እንደሆነ [4] ተነግሯል።

ደርግ ባይሆን ኖሮ ይህን መሰል ሥር ነቀል የመሬት አዋጅ ሥራ ላይ ማዋል አይቻልም ነበር [5] ተብሏል። ሆኖም ግን ንጉሠ ነገሥቱ የተካው ደርግ ባይሆንም ኖሮ ተመሳሳይ የከረረ መሬት አዋጅ መውጣቱ አይቀሬ ነበር ለማለት ያስደፍራል።

4. የአዋጁ በርካታ ስፍራዊ ጠባያት ነበሩት 

ኢትዮጵያ ትልቅና በበርካታ የሥነ-ምህዳርና መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ የበለፀገች አገር ብቻ ሳትሆን በተነባባሪነት በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣ በሕዝብ አሰፋፈር፣ በኢኮኖሚ፣ ወዘተ የተሰባጠረች ናት። በተጨማሪም የመሬት ስሪቱ፣ የጭቆና መጠኑ፣ የእርሻ መሬት ስፋትና ጥበቱ፣ የአፈር ለምነቱና መራቆቱ፣ ወዘተ ከስፍራ ስፍራ ይለያይ ነበር።

ይህ መሠረታዊ የስፍራ ልዩነት የመሬት ለአራሹ አዋጅ ገፊ ምክንያትን፣ ቅቡልነትን፣ ተቃውሞን፣ ስኬትንም ሆነ ውድቀትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አሻራውን ያሳረፈ መሆኑን ለመገንዘብ በሚከተለው መልኩ ተዘርዝሯል።

4.1 የመሬት ስሪቱ ስፍራዊ ጠባይ ነበረው: የመሬቱ ስሪቱ ገበሬውን ለድህነት እና ኢ-ፍትሃዊነትን የዳረገ ቢሆንም ችግሩ በሁሉም የኢትዮጵያ ምድር ተመሳሳይ አልነበረም። የመሬት ስሪቱ እንኳንስ በመላው አገሪቱ በጠቅላይ ግዛቶች መሃል ከፍተኛ ልዩነት ነበረው። የተማሪዎች ንቅናቄ ‘መሬት ለአራሹ’ ብሎ ሲነሳ ትኩረቱ ደቡብ ላይ ሰፍኖ የቆየውን ጭቆና መሠረት በማድረግ ነበር። የሰሜኑ እና የደቡቡ ገበሬ የሚለያየው በባላባታዊው ሥርዓት የጭቆና መጠን ብቻ አልነበረም።

የሰሜኑ ገበሬ በመሬት ጥበትና መራቆት የተሰቃየ ሲሆን የደቡቡ ገበሬ ደግሞ መሬት አልባ ጭሰኛ መሆኑ ነበር። መስፍን ወ/ማርያም [11] የመሬት አዋጁን ከነቀፈበት ምክንያቶች አንዱ ደርግ በሰሜንና በደቡብ ያለውን የመሬት ይዞታ ችግር ተመሳሳይ ማድረጉና ተመሳሳይ መፍትሔ መስጠቱ ነው።

የፓርላማ አባላት በከፍተኛ ደረጃ የንጉሠ ነገሥቱን የመሬት ስሪት የሚደግፉና በርካቶቹ የመሬት ከበርቴ ቢሆኑም ሰሜኑንና ደቡቡን ክፍል የሚወክሉት የፓርላማ አባላት ስፍራዊ ጠባይ ነበራቸው። እንደ ዓለምአንተ [1] ትውስታ ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ተመርጠው የመጡት የፓርላማ አባላት ለባለመሬት ጪሰኛ-ግንኙነት ረቂቅ አዋጁ ወገንተኛ የነበሩ ሲሆኑ ከደቡብ ኢትዮጵያ ተመርጠው የመጡት የፓርላማ አባላት ግን ከፍተኛ የመሬት ባለንብረቶች ነበሩና የረቂቅ አዋጁ ፍጹም ተቃዋሚ ነበሩ።

4.2. የሜካናይዜሽኑ ስርጭትና ጣጣ ሥፍራዊ ጠባይ ነበረው: ሜካናይዝድ እርሻ የምርት ዕድገትን ለማሳደግና ለማዘመን የሚረዳ ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ሥርጭቱም ሆነ በተጓዳኝ ያስከተለው መዘዝ ሥፍራዊ ጠባይ ነበረው። በሜካናይዜሽኑ ሳቢያ ገበሬው ከቤትና ንብረቱ መፈናቀሉ እጅግ የበረከተው በደቡብ ነበር።

ከ1940ዎቹ ጀምሮ ሜካናይዜሽን በአዋሽ ተፋሰስ (የተንዳሆ ጥጥ እርሻ፤ የወንጂ እና የመተሃራ የስኳር ፋብሪካ) ሲስፋፋ ዘላኖችን በማፈናቀል ተጀምሮ በቀጣይነትም በሰላሌ፣ በአድአ፣ በጭላሎ፣ በሻሸመኔ ወዘተ አካባቢዎች ተስፋፍቷል። ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች ሲስፋፉ የደሃው መሬት ቤቱ ሳይቀር በቡልዶዘር እየተጠራረገ ከይዞታው ተነቀሏል።

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመሬት ለአራሹ ጥያቄ እየበረከተ ሲመጣ “ይህ ነገር ጥያቄ ሊያስነሳብን ይችላል” በሚል ስጋት የልዑል አስራተ ካሳ ቤተሰቦች ጭሰኞቻቸውን ሰላሌ ውስጥ በሁለት ወረዳዎች ከነበሩበት መሬቶቻቸው ነቅለዋቸው ወደ አምቦ፣ ግንደ ብረት፣ አርሲ፣ ባሌ፣ በመሄድ ባገኙት ክፍት ሥፍራዎች እንዲሰፍሩ ተገደዋል [5]። በሰላሌ አካባቢ ገበሬው ከመሬቱ ተፈናቅሎ አዲስ ሕይወት ለመመስረት ወደ ተለያየ ሥፍራ በእግሩ ጉዞ በጀመረ ጊዜ ታሪካዊ በሆነ እንጉርጉሮ:

“ባለርስቱ ወጣሁልህ፣ ባለርስቱ ወጣሁልህ፣ 

አይጥ ጭሰኛ ከሆነልህ፣ ዳዋው (ሙጃው) ጎረቤት ከሆነልህ፣ 

ዝንጀሮ ጅጊ (ደቦ) ከወጣልህ፣ 

ከሃገር ወጣሁልህ፣ ባለርስቱ …” 

እያለ እንደሚቀጥል ፋሲካ ሲደልል (2014: 76) በልጅነቱ ይሰማው እንደነበረ ያስታውሳል።

የደቡቡ ክፍል የጭሰኝነት ሥርዓቱን በተወሰነ መልኩ ሚዛኑን ጠብቆ በመሬቱ ተረጋግቶ የቆየ ቢሆንም የሜካናይዜሽን እርሻ ሲጀመር ቀድሞ የነበረው ሚዛን በመዛነፉ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።

ሜካናይዜሽን እርሻ ሲስፋፋ ምርታማነትን ከማበልፀግ ባሻገር ትኩረቱ ስፍራው በነበረ የጪሰኛ ሕይወት ላይ ባለመሆኑ የበርካታ ደቡብ ጭሰኞች ያለምንም ማስጠንቀቂያና ማካካሻ አፈናቅሏል፤ በተማሪው ንቅናቄ ትኩሳት ላይ ነዳጅን አርከፍክፏል፤ ደርጉ ወደ ፖለቲካ ዘው ብሎ እንዲገባም በሩን ወለል አድርጎለታል።

ከ1959 ዓ.ም እስከ 1966 ዓ.ም ብቻ እስከ 5,000 ገባር ቤተሰቦች በሜካናይዝድ እርሻ ሳቢያ ከመሬታቸው ተፈናቅለዋል [6]። በሜካናይዜሽን ሳቢያ የተፈጠረው የጪሰኛው ይህወት መቆርቆዝ እና በአንዳንድ ጭሰኞች የተካሄደው አመጽ [14] ስፍራዊ ጠባይ እንደነበረው መረዳት ይቻላል።

4.3. ገበሬው የመሬት አዋጁን የተቀበለበት ፍጥነት ስፍራዊ ጠባይ ነበረው: የመሬት ከበርቴውና አራሽ ገበሬው የመደብ ተቃርኖ የነበራቸው ቢሆንም በሰሜኑ እና በደቡቡ የሚታየው የተቃርኖ መጠን እኩል አልነበረም። የሰሜኑ ገበሬ ለባላባቱ የሚከፍለው ከደቡቡ ገበሬ አነስተኛ ነበር።

ምንም እንኳ በሰሜኑ እስከ 15% ጭሰኛ የነበረ ቢሆንም ለባላባቱ እንዲከፍል የሚጠየቀው መጠን ከአቻ የደቡቡ ጭሰኛ እጅግ ያነሰ ነበር። የሰሜኑ ገበሬ ከባላባቱ መደብ የነበረው ቅራኔ እጅግ የከረረ ስላልነበረ በሰሜን ኢትዮጵያ የመሬት ለአራሹ አዋጅ ቅበላን ቀዝቃዛና ዘገምተኛ አድርጎታል።

በ1952 የፍትሐ ብሔር ሕግ መሠረት የደቡቡ ገበሬ እስከ 75% የፍሬውን ውጤት ለባለመሬቱ ፈሰስ እንዲያደርግ ይገድድ ስለነበር የመደብ ተቃርኖው በደቡቡ እጅግ የከረረ ነበር። ለዚህም ይመስላል የደቡቡ ክፍል የመሬት አዋጁን ብቻ ሳይሆን የገበሬ ማኅበራት ምስረታና የመሬት ክፍፍሉን በሙሉ ልብ ፈጥኖ የተገበረው።

ባሕሩ [12] እንደሚገልፀው አዋጁ በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል ይገኙ የነበሩትን ጪሰኞች በላቀ መልኩ ተጠቃሚ አድርጓል። ተስፋዬ ዲንቃ [13] በሰሜኑ እና በደቡቡ ገበሬ መሀል የመሬት አዋጁ “የቅበላ ልዩነት” (enthusiasm gap) እንደነበረው መግለፃቸው ከላይ የተጠቀሰውን ሥፍራዊ ጠባይ ያጠናክራል።

4.4. የባላባቱ ተቃውሞ ስፍራዊ ጠባይ ነበረው: በርካታው የመሬት ከበርቴ የመሬት አዋጁንም ሆነ አብዮቱን ለመቀልበስ ብረት ባያነሳም ጥቂት የማይባሉ የተቆጡ የመሬት ከበርቴዎች ግብረ አበሮቻቸውን አስከትለው በመሸፈት መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ፈፅመዋል። ምንም እንኳ ያመጹት ባላባቶች የተነጠቁት ደቡብ የሚገኘውን መሬታቸውን ቢሆኑም ለሽፍትነት የመረጡት ሥፍራ ደግሞ በመሀልና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ነበር።

ብዙ የትግራይ፣ ጎጃም እና የበጌምድር እንዲሁም የተወሰኑ የወሎ እና የሸዋ አውራጃዎች ከመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነፃ ሆነው ለደርግ መንግሥት ስጋት መሆናቸው የሚያመላክተው የሰሜኑ ኢትዮጵያ ከደቡቡ የሚለይበት ሌላው ጠባይ ነበር።

4.5. የተማሪው የፖሊቲካ ጥያቄ ስፍራዊ ጠባይ ነበረው: የመሬት ለአራሹ በውስጡ የኢኮኖሚ ጥያቄ ቢኖርበትም በዋናነት ግን የፖለቲካ ጥያቄ ነበር። የመሬት ይዞታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሆኑት እነ ዘገየ እና ዓለምአንተ በአዋጁ ሽግጅት ወቅት ተሳታፊዎቹ ተራማጅ የነበሩ እንጂ የብሔር ፖለቲካ እንዳልተቀላቀለበት በቅርብ በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች የመሰከሩት ጉዳይ ቢሆንም የብሔር ጥያቄን ከመሬት አዋጁ ጋር ተንጠላጥሎ ለመጓዙ ጥቂት አመላካቾች የነበሩ ቢሆንም አዋጁ ከታወጀ በኋላ በበርካታ ሥፍራዎች ታይቷል።

አዋጁን እንደ ኖህ መርከብ የተጠቀሙበት የብሔር አራማጅ ግለሰቦችና ድርጅት እንደነበሩ ማሳያዎች ቢኖሩም እርግጠኛ ለመሆን ጠለቅ ያለ ምርምር የሚሻ ጉዳይ ነው።

የሰሜኑ ገበሬ ከባላባቱ ጋር በቋንቋ እና በሀይማኖት አንድ በመሆናቸው የመደብ ተቃርኖው የለዘበ ነበር። እንደውም አዋጁን ለኦሮሞውና ለሙስሊሙ እንጂ ለአማራ-ትግሬ ክርስቲያኑ እንዳልመጣ ተቆጥሮ ይታይ ነበር [14]። በደቡብ የነበረው የከረረ የመደብ ተቃርኖ ብቻ ሳይሆን የሀይማኖትና የቋንቋ ልዩነቶችንም ያስተናግድ ነበር።

ባላባቱ ክርስትያኖች፣ ጭሰኞቹ እስላሞች ወይንም ሀይማኖት የለሾች ስለነበሩ በባላባቱና በጪሰኛው መሃል የነበረው የልዩነት መስመር ደመቅ ያለ ነበር። በመሆኑም የመደብ ልዩነት ከብሔር ጥያቄ ጋር የተቆራኘበት ሁኔታ ሥፍራዊ ልዩነት እንደነበረው መገንዘብ ይቻላል።

እንደ ደሳለኝ [15] ከሆነ በወቅቱ ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ ብሔረሰብን ማዕከል አድርጎ የሚሽከረከር አልነበረም፤ የብሔረሰብ ጭቆናው ዋንኛ መሠረቱ የመሬት ስሪቱ ነበር።

በሌላ በኩል እንደ ደቡቡ ክፍል ጎልቶ አይታይ እንጂ በጎጃም ደጋ ዳሞት በመሬት አዋጁ ማግሥት በርካታ የሙስሊም እምነት ተከታይ አርሶ አደሮች ከቀያቸው ተባረው በመጨረሻ መንግሥት በመተከል አውራጃ ቻግኒ አካባቢ እንዳሰፈራቸው ተመስክሯል [1]። ሁኔታው የሚያስገነዝበው ከመደብ ልዩነቱ ጋር ተነባብሮ ኃይማኖታዊ ተቃርኖ እንዳስተናገደም ነው።

ደርግ የመሬት ስሪት መፍትሔ ማምጣት ማለት አብዛኛው የተገፉ እና የተጨቆኑ ብሔረሰቦችን የሚመለከት እንደሆነ አልተገነዘበም ነበር። ከላይ የተጠቀሱትን ክስተቶች መሠረት በማድረግ ላለፉት ሶስት አስርት አመታት በኢትዮጵያ ሕጋዊነት ተላብሶ በሥራ ላይ የዋለው የብሔር ተኮር ፖለቲካ የተጠነሰሰው ምናልባትም ከመሬት ለአራሹ አዋጅ ማዕቀፍ ውስጥ ነበረ? የሚል መላምትን መሠንዘር ይቻላል፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችንም ለምርምር ይጋብዛል።

በአጠቃላይ ከአዋጁ ማግስት ጀምሮ ደርጉ አቅሙ በፈቀደ የገበሬውን ሕይወት ለማሻሻል በገበሬ ማኅበራት፣ በመንደር ምስረታ፣ በሰፋፊ የሰፈራ ፕሮግራሞች፣ እና በምግብ ለሥራ የሚደጎሙ እርከን ሥራና ደን ተከላ ፕሮግራሞች፣ ወዘተ ጥረት ቢያደርግም የገበሬውን ሕይወት ከፍፁም ድህነትና ምግብ ዋስትና እጦት ሊያላቅቀው አልቻለም።

5. የኢሕአዴግ መንግሥትና የመሬት አዋጁ

ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲጨብጥ የደርግን ኢ-ዴሞክራሲና ኢ-ፍትሃዊ ሥርዓትን አስወግጄ ነፃ ገበያን በኢትዮጵያ አሰፍናለሁ ብሎ ቃል ቢገባም የገጠር መሬት ባለቤትነትን በተመከለተ ከደርጉ አልተለየም።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 የገጠርና የከተማ መሬት ባለቤትነት መብት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቱ በሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝቦች ብቻ ነው። መሬት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው ብሎ ደነገገ።

እርግጥ ነው በሂደት መሬት ማከራየትና በራስ መሬት ላይ የቅጥር ጉልበት መጠቀምን ፈቅዷል፤ መሬትን በውርስ የማስተላለፍ መብት ሰጥቷል፤ የገበሬዎችን የመሬት ባለቤትነት መብትን ለማረጋገጥ የመሬት ምዝገባ እና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሰጥቷል። ሆኖም መሬት የሚሸጥው በመቃብሬ ላይ ብቻ ነው ብሎ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ዘልቋል።

የደርግ ሥርዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ ከዳር አስከዳር እኩል ባለመሬት ለማድረግ አዋጅ አወጀ፤ ርስትንም ማደሪያንም ሽሮ የመሬት ባለቤትነትን በዜግነት ላይ ተከለ። የወያኔ ሥርዓት ሲመጣ የገጠር መሬትን በፖለቲካ ታማኝነት ደለደለ ብሎ መስፍን ወ/ማርያም [11] መኮነኑ ለተነሳው ጉዳይ ገላጭ አባባል ይሆናል።

የኢሕአዴግ/ብልፅግናም ሆነ ሌሎች የብሔር ፖለቲካ ቡድኖች የመሬት ባለቤትነት ክርክርን ከብሔር ፖለቲካ መነፅር ብቻ እንዲመዘን ሞግተዋል። በተቃራኒው ጉዳዩን ከኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ መርህ አንፃር መሞገት የድሮ ሥርዓት ናፋቂ የሚል ስያሜን የሚያሰጥ ጉዳይ ሆኗል።

መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም የሚለው መፈክር እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ሰፊ የእርሻ መሬቶቿን ለውጭ ባለሀብቶች ከ8 ዶላር (በሄክታር) ጀምሮ ሆኖ እስከ 99 ዓመታት ድረስ በሚፀና የሊዝ ውል በገፍ አከራይታለች። ለመሬት ተከራዮቹ “የክፍለ ዘመኑ ስምምነት” ቢባልም "መሬት ነጠቃ" (land grab) የሚለው አጠራር የበለጠ ይገልፀዋል [16]።

ኢሕአዴግ ለገበሬው የተለየ ተቆርቋሪነትና አጋርነት አለኝ በማለት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲዬ የግብርና-መር ነው ብሎ፤ የተለያዩ የግብርና እና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሞችን ዘርግቶ፣ የሳሳካዋ ግሎባል 2000 የተሰኘ አረንጓዴ አብዮት ቀመስ ፕሮግራም አራምዶ፤ በአንድ በኩል የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሥር የነበሩ አንጋፋዎቹን የእርሻ ኢኮኖሚክስ እና የእርሻ ምህንድስና ዲፓርትመንቶችን ያለ አሳማኝ ምክንያት ዘግቶ፣ በምትካቸው የእርሻ አክስቴንሽን ኮሌጆችን በአገሪቱ አስፋፍቶ፣ የኢትዮጵያ እርሻ ወኪሎች ብዛት ከቻይና እና ከህንድ ቀጥሎ በዓለም በሶስተኛ ደረጃ እንዲገኝ ቢያደርግም ይህ ሁሉ ጥረት ተደማምሮ በቅድመ መሬት አዋጁ ዘመን የጭላሎ እርሻ ልማት (ካዱ) ያሳየውን ዓይነት ውጤት እንኳ አላስገኘም።

6. የአዋጁ ትሩፋትና ጉዳት

የመሬት አዋጁ እንደታወጀ ወደር የማይገኝለት ሕዝበኝነትን ተጎናፅፏል። በወቅቱ የማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለም በተማሪው እንደፋሽን ይታይ ነበር። ይህ ርዕዮተ ዓለም ቀደም ብሎ በሩሲያ፣ ቬትናም፣ ቻይና፣ ወዘተ መሬት ከበርቴዎች ላይ ግዳይ ጥሎ ዝናው ካፅናፍ እስካፅናፍ ናኝቶ ነበርና የ1967ቱ ሥር ነቀል አዋጁን መደገፍ ማለት የሞራል ልዕልና እንደመጎናፀፍ የሚቆጠር ጉዳይ የነበረ ይመስላል። ባለ መሬቱን ባንድ ጀምበር ባዶ አስቀርቶ ገበሬውን የመሬት ባለቤት የሚያደርግ አዋጅ እንደ ምሉዕ በኩለሄ ተደርጎ ተወስዷል።

በተለይም በደቡቡ ክፍል ደርሶ የነበረው እጅግ አሰቃቂ በደል ተደጋግሞ ለተቃውሞ ማጠናከሪያነት ሲወሳ ስለከረመ የደቡቡ ገበሬ አዋጁን እጁን ዘርግቶ መቀበሉ አይደንቅም። አዋጁ የፈጠረው የመንፈስ ኩራትም ዛሬም ድረስ ህያው ሆኖ በተለይም በደቡቡ ክፍል ፖለቲከኞች እንደ ትልቅ ድል የሚወሳ ጉዳይ ነው።

የአዋጁ ሌሎች ትሩፋቶች [1] ደግሞ በመሬት ክርክር ሳቢያ በየፍርድ ቤቶች ይጠፋ የነበረው ጊዜ ፈፅሞ እንዲወገድ መደረጉ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የግብር ዓይነቶች መወገዳቸው፣ “አርሶአደሩ የጉልበቱን ፍሬ ማንም ሳይካፈለው ለራሱና ለቤተሰቡ ፍጆታ ብቻ ማድረጉ” ናቸው።

ሌላው ይቅርና በመሬት አዋጅ ሳቢያ እነ ሶቪየት ሕብረት አያሌ ቁጥር ላለው ሕዝብና ለከብቶች ውድመት ተጋልጠው ሳለ፣ ተመሣሣይ ቀውስ በኢትዮጵያ አለመከሰቱ ሌላው የተመሰከረ የአዋጁ ስኬት ነው።

ከላይ የተጠቀሱት ቀላል የማይባሉ ትሩፋቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ውሎ አድሮ የመሬት አዋጁ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን አስከትሎ እንደነበር ያለፉት ሃምሳ ዓመታት እንደ መስታወት ያሳዩናል።

አንደኛ፤ የደርጉም ሆነ የመሬት ይዞታ ባለሥልጣናት የመሬት አዋጁ ባላባቶችን አላገለለም ይላሉ። ለምሳሌ ሚኒስትር ዘገየ አስፋው [3] የመሬት ከበርቴው ከዚህ ነው ከዚያ ነው የመጣኸው ሳይባል የድርሻውን እንደሌላው ገበሬ ማግኘት ይችላል ሲል ዶ/ር ያየህ ይራድ ቅጣው [17] ደግሞ “ባላባቶች ከአገር ውጡ አልተባሉም” ብሎ ይመሰክራል። ሆኖም በተግባር የታየው ሌላ ነበር።

በበርካታ የደቡብ አካባቢዎች የእርሻ ማሳሪያዎችና በሬዎች ያለ ካሳ ተወርሰዋል፤ ከአዋጁ ቀደም ብሎ ተመርቶ የነበረና በጎተራ የነበረ እህል እንኳ የተወረሱባቸው ሥፍራዎች አሉ፤ ከቀያቸው የመባረር እና የመመገደል ዕጣ የደረሳቸው ዜጎችም ነበሩ።

ሁለተኛ፤ ከመሬት አዋጁ ቀደም ብሎ ከሰሜንና መሃል ኢትዮጵያ እየተነሱ ገበሬዎች ወደ የደቡብ ምዕራብ ወቅትን እየጠበቁ ለቡና ለቀማ ይመጡ የነበር ቢሆንም ከአዋጁ በኋላ ይህ የፈረቃ ምልልስ (seasonal migration) ተቋርጧል።

አንድም አዋጁ አርሶ አደር ሠራተኛ መቅጠርን በመከልከሉ፣ ሌላም በገበሬ ማኅበራት ያልታቀፈ በእርሻ ሥራ ሊሰማራ ስለማይችል ነበር። አልፎ ተርፎም በቡና ለቃሚ ዜጎች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት እየተባባሰ መጥቶ ነበር። እንደ ውድ [18] ምሥክርነት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመሬት አዋጁ “የመሬት ብሔርተኝነትን” አስፍኖ ነበር።

ሶስተኛ፤ ከአዋጁ በኋላ የገበሬው ምርታማነት እንደሚጨምር ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም በተግባር አልታየም። መሬት በገበሬ ማኅበራትና በህብረት ሥራዎች መተዳደሩ የሥራ ፉክክርን፣ ፈጠራን፣ እና ምርታማነትን በእጅጉ አቀጭጮታል። የመሬቱ ህጋዊ ጣራው አስር ሄክታር ብቻ በነበረበት ሁኔታና ከ61 በመቶ በላይ የሚሆኑ የአርሶ አደር ቤተሰቦች ከአንድ ሄክታር ያነሰ መሬት በያዙበት አገር የእርሻ ምርታማነትን ለማሳደግ ማቀድ ጉም እንደ መጨበጥ ሆኖ ቆይቷል።

መስፍን [11] የመሬት አዋጁን ሲወቅስ ቀደም ብሎ ተጀምሮ የነበረውን ከፍተኛ የትላልቅ የእርሻ ዕድገት ማገዱ ነው ይላል፤ ሌሎች በርካቶችም ሐሳቡን ይጋሩታል። ገበሬው እስከ 75% የእርሻ ምርት ውጤቱን ለባላባቱ እንዲሰጥ ይገደድ ነበረና ከአዋጁ በኋላ ገበሬው እጅ የሚገባው የምርት መጠን በሶስት እጥፍ (300%) ማደግ ነበረበት። ምንም የተሻለ ነገር አለመገኘቱ ከአሮጌው ጉልታዊው ሥርዓት ሌላ የገበሬውን ሕይወት ቀስፎ የያዘ ሌላ አንኳር ጉዳይ ነበርን ያስብላል።

አራተኛ፤ ገበሬው የመሬት ባለቤትነት ሲሆን መሬቱን ይንከባከባል፣ ድርቅና ረሃብ ተጋላጭነቱን ይቀንሳል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም ከአዋጁም ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል። ገበሬው ጉልበቱንም ሆነ ገንዘቡን በመሬቱ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ከረዥም ጊዜ በኋላ የሰብል ምርታማነትን እና የአካባቢ ልማትን ያመጣልኛል ብሎ ለመተማመን አልቻለም።

የእርከን፣ የፍሳሽ ቦዮች፣ የደን ማልማት ወዘተ የሚደረግ ተነሳሺነትን ማዳከሙን በርካታ ጥናቶች መስክረዋል። በዚህ ሳቢያ፣ የመሬት የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ ተመናምኗል፤ የምግብ ዋስትናውም እያሽቆልቁሏል፤ ቀላል የማይባል ገበሬ በምግብ እርዳታ ላይ ሕይወቱ ተንጠላጥሏል።

አምስተኛ፤ ደርጉ የመሬት አዋጁን አስፈላጊነት ሲያስረዳ የንጉሠ ነገሥቱ የመሬት ስሪትና ኢ-ፍትሃዊነት ለወሎው አስከፊ ረሃብ አስተዋፅዖ አድርጓል ብሎ ፈርጆ ነበር። የመሬት አዋጁ በታወጀ በአስር ዓመቱ በ1977 ዓ.ም ከቀድሞው የባሰ አሰቃቂና አስከፊ ረሃብ በኢትዮጵያ ሲከሰት ሌሎች በርካታ ጉዳዮች መታየት እንደሚገባ አመላካች ነበር።

ድርቁን በዘለቄታው ለማስወገድ ተብሎ የተካሄው የሠፈራ ፕሮግራም ያለ በቂ ዝግጅት የተከወነ በመሆኑ ትልቅ ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሎ ሌላው ይቅርና ቀድሞ የመሬት አዋጁን በአድናቆት የተቀበሉት ገበሬዎች ጭምር ቅር ተሰኝተው ነበር።

ስድስተኛ፤ መሬት ከባላባቱና መዳፍ ተላቀቀ ቢባልም ገበሬው በመሬቱ ላይ ምንም አይነት ውሳኔ እንዳይሰጥ አድርጎ መንግሥት ራሱ የመሬት ከበርቴ ሆኖ ቁጭ ብሏል። የገበሬ ማኅበራትን በማስገደድ እህል ከገበያ በታች በሆነ ዋጋ ለእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት እንዲሸጥ አስገድዶ አርሶ አደሩ የተጣለበትን ኮታ ማሟላት ሳይችል እየቀረ ከብቶቹን ሸጦ ከገበያ በውድ ዋጋ ገዝቶ በኪሳራ ለኮታ ማሟያ የሚያስረክብባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ። በሌላ ቋንቋ የገበሬው ሰቆቃ በሌላ ገፅና ቁመና ቀጥሎ ነበር።

ሰባተኛ፤ በመሬት ለአራሹ ሳቢያ የመሬት ክርክርና የፍርድ መጓደል አበቃለት ተብሎ የተነገረ ቢሆንም ከአዋጁ በኋላ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሰፈነው የመሬት ነክ ፍርድ ይግባኝ የሌለው፣ ብያኔ የሚሰጠው ደግሞ የሕግ መሠረታዊ ዕውቅትና ልምድ በሌላቸው የገበሬ ማኅበራት ተመራጮች ሆነ። የፈለገ ውሳኔ ገበሬው ላይ ቢጣል “አሜን” ብሎ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም።

ስምንተኛ፤ መሬት አልባነት በቅድመ አዋጁ ዘመን አንዱ ችግር ነበረ፤ ከአዋጁ በኋላም አልቆመም። አዋጁ ከሥነ-ሕዝብ ጋር የተያያዙ ለውጦችን ግምት ውስጥ ባለማስገባቱ መሬት አልባነት ቀጣይነት እንዲኖረው አድርጎታል። የእርሻ መሬት ዕጥረት ችግርን ለመቅረፍ ሲባል የግጦሽ መሬቶች፣ዳገታማ መሬቶች፣ ደኖች እና ሌሎች በቀላሉ የሚጎዱ ስነ ምህዳሮች ለእርሻ ሥራ በመዋላቸው በተለይ የሰሜን ደጋማ አካባቢዎች ከፍተኛ ለሆነ የአፈር መሸርሸርና የውሀ ምንጮች መድረቅና ለአካባቢ መራቆት ተጋልጠዋል።

ዘጠነኛ፤ ቀድሞ የነበረው የመሬት መሸንሸን ከአዋጁም በኋላ ተባባሰ እንጂ አልቀነሰም። የገበሬ ማኅበራቱ ለመሬት አልባ ወጣቶች ሲባል ያልተቋረጠ የመሬት ክፍፍልና ሽንሸና ያደርጉ ስለነበር የነፍስ ወከፍ ይዞታ መጠን ከግማሽ ሔክታር በታች ሆኗል።

7. ማጠቃለያ 

በዚህ ፅሁፍ በ1967 ዓ.ም ከነበረው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካ ሁኔታ አንፃር የመሬት አዋጁ አይቀሬ እንደነበረ The writing is on the wall እንዲሉ፤ የአዋጁ በሚረቀቅበት ወቅት ፅንፈኝነቱን በማለዘብ ለገበሬው የተሻሉ ዕድሎችን ማቅረብ ይቻል እንደነበረ፤ አዋጁ ጠቃሚም ሆነ ጎጂ ገፅታዎች እንዳሉት፤ ዛሬም የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ካለ ሊሻሻል የሚችልባቸው መንገዶች እንዳሉ ተንጸባርቋል።

የመሬት አዋጁ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ወደ 23 ሚሊዮን የሚገመት ገበሬ ሕይወትን፣ ዛሬ ደግሞ እስከ 80 ሚሊዮን የሚገመት ገበሬን ሕይወትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚዘውረው በመሆኑ አሁንም ቢሆን ሊፈተሽና ሊሻሻል የሚገባው ጉዳይ ነው።

የመሬት አዋጁ ሲረቀቅም ሆነ ሲታወጅ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የተጣጣመ አለመሆኑ ትልቁ ሥህተት ነበር። የሰሜኑም ሆነ የደቡቡ አርሶ አደር የገጠመው ችግር የተለያየ ሆኖ ሳለ አዋጁ ለሁሉም የአገሪቱ ክፍል አንድ አይነት የፈውስ መድሃኒት ማቅረቡ ፋይዳውን አሳንሶታል። ለሁሉም አይነት ምስማር አንድ አይነት መዶሻ አያገለግልምና።

ሆኖም አዋጁን በግርድፉ “አላዋቂው ደርግ ያወጀው” [11] ብሎ ማጣጣልም ፍርደ ገምድል ያሰኛል። ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የደርግ አባላት እንኳ እርግጠኛ ባልሆኑበት ሁኔታ አዋጁን ሰፊው ማኅበረሰብ ላይ መሞከሩ (social experimentation) ትልቅ ቁማር ነበር። አዋጁ የእርሻ መሬቱን ከባላባቱ መዳፍ አላቀቀ ቢባልም ውሎ አድሮ መሬቱ በመንግሥት ሙሉ ቁጥጥር በመዋሉ የ “መሬት ለአራሹ” ምላሽ ዛሬም ከሃምሳ አመት በኋላ ያልተጨበጠ ጉም ሆኖ ቀርቷል።

በውጤቱም ከተበላለጠ ድህነት ወደ እኩል ድህነት ሽግግር ተደርጓል። የመሬት ዋስትና እጦቱ ሳቢያ ገበሬው ከገጠር እርሻው እንዳይርቅ ታግቷል፣ የእርሻ መሬቱ በውርስም ሆነ በሌላ እየተሸነሸነ ለዘመናዊ እርሻ እንዲያመች ሆኗል። ምናልባትም መሬቱ ባንድ ሥሙ የመንግሥት ነው ተብሎ ቢታወጅ ኖሮ መንግሥት በቀጥታ ተጠያቂነት ኖሮበት አዋጁን ለማሻሻል በፍጥነት ይነሳሳ ነበር።
ከተበላለጠ ድህነት ወደ እኩል ድህነት ሽግግር ተደርጓል።
ታውቆም ይሁን ሳይታወቅ የመሬት ጉዳይ ከብሔር ማንነት ጋር ተጠላልፎ ተቋጥሯል። በተለይም ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የመሬቱን ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ ለማስተካከል የሚደረግ ሙከራ የብሔር ፖለቲካውን ነርቭ እየነካካ የመፍትሔውን መንገድ አጥብቦታል።

ከመሬት አዋጁ በኋላ የደርጉም ሆነ የኢሕአዴግ መንግሥታት የገበሬውን ችግር ላንዴና ለመጨረሻ ይቀርፋሉ ያሏቸውን የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርፀው በርካታ ያገር በጀት፣ የብድርና የዕርዳታ ሀብትን አፍስሰዋል።

በጥቂት ማሳዎች ላይ የፕሮግራሞቻቸውን ስኬቶች በሚዲያ ቢያሳዩም የሰፊው ገበሬ ችግር ሲቀንስ አልታየም። ዛሬም ገበሬው የዝናብ ጥገኛ ነው። ከ20 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ በምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ ሆኖ ከመሠረታዊ የኑሮ ደረጃ በታች ይኖራል።

የመሬት ፖሊሲና የብሔር ጉዳይ ህጋዊ ፍቺ ካላደረጉ እና በገጠር መሬት ላይ የተከማቸው የገበሬ ቤተሰብ ወደ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ሽግግር ካልተደረገ በቀር ችግሩ ተባብሶ የበለጠ ድህነት፣ የምግብ ዋስትና ማጣት፣ ተረጂነት ይነግሳል።

ስለሆነም ይህን 50ኛ የመሬት ለአራሹ አዋጅ የወርቅ ኢዩቤልዩ ተንተርሶ በቀጣይ ሊከወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየቱ መልካም አጋጣሚ ስለሆነ ሊባክን አይገባም።

ምንጮች

[1] ዓለምአንተ ገብረሥላሴ (2024 እኤአ)። ትውስታዎቼ: ስለመሬት ይዞታና የተለያዩ ፖለቲካዊና አገራዊ ገፅታዎች። ዘ ሬድ ሲ ፕሬስ።

[2] ደረሰ አየናቸው (2013)። ሰለሞናውያን፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ (1262-1521)

[3] ዘገየ አስፋው (የካቲት 2016 ዓ.ም)። ከNBC Ethiopia ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ። ዘገየ አስፋው የመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ባልደረባና በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የጭሰኛ ጥናት ኃላፊ፤ በደርግ ዘመን ደግሞ ሚኒስትር ነበሩ።

[4] አንዳርጋቸው አሰግድ (2020 ዓ.ም)። ባጭር የተቀጨ ረዥም ጉዞ፡ መኢሶን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል ውስጥ። ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት።

[5] ፍስሐ ደስታ (2008 ዓ.ም)። አብዮቱና ትዝታዬ። ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት።

[6] ኮኸን = Cohen, J. M. (1987). Integrated rural development: the Ethiopian experience and the debate. Nordic Africa Institute.

[7] ብርሃኑ ባይህ (2013)። ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ። የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ። አዲስ አበባ።

[8] ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ (2013 እኤአ)። እኛና አብዮቱ። ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት።

[9] ፋሲካ ሲደልል (2014 ዓ.ም)። ሻምላው ትውልድ። ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት። አዲስ አበባ።

[10] ክፍሉ ታደሰ (1993 ዓ.ም)። ያ ትውልድ ቅጽ 3፡ የለውጥ ማዕበል በኢትዮጵያ የኢሕአፓ ታሪክ፡ 2ኛ ዕትም

[11] መስፍን ወልደማርያም (2012)። መሬት፣ መሬት፣ አንድ። ኢትዮ አንድነት ድረገፅ።

[12] ባሕሩ ዘውዴ (1999)። የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ። አዲስ አበባ።

[13] ተስፋዬ ዲንቃ = Tesfaye Dinka (2017)። ETHIOPIA: The Derg Years: An Inside Account. Tsehay Publishers.

[14] ኦታዋይ = Ottaway, M. (1977). Land reform in Ethiopia, 1974-1977. African Studies Review, 20(3), 79-90.

[15] ደሳለኝ ራህመቶ (2024 እኤአ)። ቢቢሲ አማርኛ (19 የካቲት 2024)። መሬት ለአራሹ፡ የገጠሪቱን ኢትዮጵያ መልክ የቀየረው የተማሪዎች ንቅናቄ።

[16] ደሳለኝ ራህመቶ= Dessalegn Rahmato (2011). Land to investors: Large-scale land transfers in Ethiopia (No. 1). African Books Collective.

[17] ያየህ ይራድ ቅጣው። የደርጉ ሚኒስትር የነበሩ የካቲት 2016 ዓ.ም ከNBC Ethiopia ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ።

[18] ውድ = Wood, A. P. (1983). The decline of seasonal labor migration to the coffee forests of South-West Ethiopia. Geography, 68(1), 53-56.


ዳንኤል ካሳሁን (ፒ ኤች ዲ) በመሬት-ነክ ጉዳዮች የተለያዩ መጣጥፎችን የሚያበረክቱ ሲሆን በኦስተን / ቴክሳስ የጂኦስፓሻል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው ይገኛሉ፡፡

*** ይህ መጣጥፍ ቀደም ብሎ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የካቲት 23 ቀን 2017 / ማርች 2 ቀን 2025 ታትሟል።



Share

Recommended for you